የተፈጥሮ ጸጋዎች ላይ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሠረት ይጥላሉ – አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

መስከረም 20/2016 (አዲስ ዋልታ) የተፈጥሮ ጸጋዎችን ከሰው ኃይል ጋር በማስተሳሰር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በጅማ እና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን በዋናነት በአካባቢዎቹ የሚከናወኑ የሌማት ትሩፋት፣ እንዲሁም የግብርና ሥራዎችን የጎበኙ ሲሆን፤ በጅማ ከተማ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት የሚከናወነው የቱሪዝም ልማት ሥራም ተመልተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በጉብኝታቸው በጅማ ዞን ሕዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው በቡና፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቱሪዝም ልማት አበረታች ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ይህም የፌደራል መንግሥት ከክልሎች ጋር በመቀናጀት እያከናወናቸው ያሉ የልማት ሥራዎች በውጤታማ መንገድ ላይ መሆናቸውን ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ መሰል የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ጠቁመው ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም አፈ- ጉባዔው አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በርካታ ፈተናዎችን በጋራ በማለፍ አብሮነታቸውን አስጠብቀው መቀጠላቸውን አስታውሰው፤ ይህንን የሕዝብ አብሮነት በልማት ሥራዎች በማስተሳሰር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በሌማት ትሩፋትና ቱሪዝም ልማት የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አባ ዱላ ገመዳ በበኩላቸው፤ በጉብኝታቸው በጅማ ከተማና አካባቢው በርካታ አዳዲስ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም ከዚህ ቀደም በአካባቢው የማይመረቱ እንደ ሩዝ ያሉ ምርቶችን በስፋት ማልማት መቻሉን ጠቅሰው፣ የቡና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ረገድም ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይ በጅማ ከተማ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ አቅም እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡

በሌማት ትሩፋትና ግብርና ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት በማሳለጥ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከዚህ አኳያ አመራሩ በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን በሁሉም አካባቢዎች በማስቀጠል ረገድ ይበልጥ መሥራት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡