የቱርክ ባለሃብቶች በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) የቱርክ ባለሃብቶች በአፋር ክልል የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ጥሪ አቀረቡ።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፒራክ አልፒ ከአፋር ክልል  ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሰመራ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ቱርክና ኢትዮጵያ የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ቱርክ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት አጀንዳዎችና ኢንቨስትመንት ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

የቱርክ አምባሳደሮች በተለያዩ ጊዜያት በአፋር ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸው ከዚህ በፊት በክልሉ በነበረው ድርቅ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት በተግባር አረጋግጠዋል።

የዛሬው አምባሳደሯ ጉብኝትም ይህን ወዳጅነት የሚያስቀጥል መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ቱርካዊያን ባለሃብቶችም በክልሉ በጨው አይወዳይዜሺን እየተሳተፉ ሲሆን በተጨማሪም በሪልእስቴትና ኬሚካል ኢንዱስትሪ መስክም ኢንቨስት ለማድረግ ቦታ የወሰዱ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፒራክ አልፒ በበኩላቸው የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት  የበለጠ ለማጠናከር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

አክለውም ቱርክ በኢትዮጰያ የልማት እቅዶችን ከመደገፍ ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች  አጫጭር የሥራ ላይ ስልጠና ድጋፍ አያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።