የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለተፋሰሱ አገራት እውነተኛ የትብብር ማዕከል ሆኖ ይቀጥላል – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

ሐምሌ 15/2013 (ዋልታ) – ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዓባይ ወንዝ የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጭምር የትብብር ማዕከል ሆኖ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ  ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው በአረብኛ ቋንቋ ባጋሩት መልዕክት ኢትዮጵያ ቀድም ብላ ባስቀመጠችው እቅድ መሰረት በሐምሌ ወር መግቢያ ላይ ሁለተኛውን የህዳሴው  ግድብ ሙሌት ያለምንም እንከን ማከናወኗን አመልክተዋል፡፡

የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በተከናወነው ሙሌት የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ተፅዕኖ በማይፈጥር መልኩ በጥንቃቄ መከናወኑን እና ይልቁንም ከፍተኛ መጠን ያለውን ጎርፍ መቆጣጠር በሚያስችል መልኩ መፈፀሙን እንዲገነዘቡም በመልዕክታቸው ጠይቀዋል፡፡

ሁለተኛው ዙር የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ወዲፊትም ቢሆን በአንዳቸውም የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉዳት እንደማያስከትል ጭምር በመገንዘብ፣ ይልቁንም  ግድቡ በተፋሰስ  አገራት መካከል የእውነተኛ ትብብር ምንጭ ሆኖ እንደሚቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጠይቀዋል፡፡