የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገለጸ

ዶክተር በለጠ ብርሃኑ

ግንቦት 12/2013 (ዋልታ) – 650 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገልጿል።

የኃይል መሥመር ዝርጋታው ግድቡ ከተገነባበት ጉባ አንስቶ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት አስከሚገኝበት ሆለታ ድረስ የተዘረጋ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኃይማኖት አባቶችና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ግድቡን በተመለከተ ዛሬ ውይይት አድርጓል።

የግድቡ ተደራዳሪዎች ቴክኒክ ቡድን አባል ዶክተር በለጠ ብርሃኑ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የግድቡ ግንባታ በመልካም ደረጃ ላይ ይገኛል።

አሁን ላይ ከግንባታና ከኮንክሪት ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚሰራው የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ሥራ 91 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱንም ነው የጠቆሙት።

የግድቡ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው 54 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም የኃይድሮሊክ ስትራክቸር ደግሞ 55 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱን ነው የገለጹት።

ከዚህ ጎን ለጎን ከጉባ እስከ ሆለታ የሚደርሰው የ650 ኪሎ ሜትር የግድቡ ኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ነው ያሉት።

ግድቡ ቅድመ ምርት ሲጀመር ወዲያውኑ ኃይል እንዲያስተላልፍ ወደ ሥራ እንደሚገባም ከኢዜአ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።

በተጓዳኝም የግድቡ ሁለት ተርባይኖች የቅድመ ኃይል ምርት በመጪው ክረምት መጨረሻ አካባቢ እንደሚጀምርና ለዚህም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዶክተር በለጠ አስታውቀዋል።