መጋቢት 24/2013 (ዋልታ) – ለኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከምንም በላይ በቀዳሚነት የሚጠቀስበት ትልቁ ምክንያት ታሪካዊ ትርጉም እና ኢኮኖሚያዊ ፍቺ በመያዙ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሠረት ድንጋይ ለተጣለበት 10ኛ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልክዕክት በማህበራዊ ገጻቸው አአስተላልፈዋል፡፡
ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ የልማት እና ዕድገት ውጥኗን በፍጥነት ለማስቀጠል ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም መሰረት ከሚጥሉ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ፣ “ለዘመናት ያለአንዳች ፋይዳ ሲፈስ የነበረው ታላቁን የአባይ ወንዛችንን ለሃይል ማመንጫነት ሙሉ በሙሉ በራሳችን ሃሳብ፣ ጉልበት እና ገንዘብ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠን አሁን የግንባታውን ሂደት ወደ ማገባደጃ ምዕራፍ መሸጋገራችን ታሪካዊ ትርጉሙን ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል“ ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽለው ከመሆኑ ባሻገር፤ ለታችኛው ተፋሰስ ሃገሮች እና ለቀጠናው ሃገራት በሃይል ልማት ጠንካራ ትስስር መፍጠር ማስቻሉ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፍቺ ይይዛል ብለዋል አቶ ደመቀ።
ባለፉት የግንባታ ዓመታት በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ዙሪያ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት እና የዕርምት ዕርምጃዎችን በትኩረት በመውሰድ ግንባታው ወደ ማገባደጃ ምዕራፍ ለማሸጋገር መቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በእነዚህ ዓመታት ግድቡን አስመልክቶ የተለያዩ ፍላጎቶች እና ስሜቶች በስፋት ሲንፀባረቁ የከረሙ ቢሆንም፤ በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ በመርህ ላይ በተመሰረተ ድርድር ግልፅነትን ለመፍጠር እና ከስምምነት ለመድረስ አያሌ ጥረቶች ተደርገዋል ብለዋል ሚኒስትሩ።
“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የመሰረተ ድንጋይ ከተጣለበት ቀን አንስቶ አሁን ለደረሰበት ደረጃ በሃገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖረው ህዝባችን ያበረከተው የፋይናንስ እና የሞራል ድጋፍ ታሪክ መቼም አይዘነጋውም” ብለዋል አቶ ደመቀ።
ሚኒስትሩ፣በታችኛው ተፋሰስ አገራት የግድቡን ግንባታ ተከትሎ የሚደመጡ ፍላጎቶች በድርድር እልባት እንዲያገኙ ፍትህ እና እውነትን በማንገብ በሀገር ቤትና በዓለም አደባባይ ድምፃችሁን በማሰማት ለሃገር ሉዓላዊነት ጥብቅና የቆማችሁ ወገኖቻችን ውለታችሁ በትውልድ መዝገብ በደማቁ ተጽፎ እስከወዲያኛው ይዘልቃል ብለዋል።
“ባሳለፍናቸው ዓመታት በጠንካራ የሃገር ፍቅር ስሜት የታየው ህዝባዊ ተሳትፎ እና ንቅናቄ ለቀሪ የፕሮጀክቱ ስራ ስኬታማ አፈፃፀም ድጋፋችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል” ሚኒስትሩ።
አቶ ደመቀለግድባችን ስኬትና ለሀገራችን ሉዓላዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብረን የምንቀሳቀስበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
“ሀገራችን በሁለት አቅጣጫ ፈተናዎች እየገጠሟት ነው፤ በአንድ በኩል የከፋ የሉዓላዊነት ጥቃት በመፈፀም ሃገራችንን ለአደጋ ተጋላጭ ከማድረግ ጀምሮ ዜጎችን በማንነታቸው መጨፍጨፍ፣ ማፈናቀል ተረጋግተው በሰላም እንዳይኖሩ በማድረግ፣ ከውጭ እየመጣ ያለውን ጫና በአንድ ልብ ሆነው እንዳይመክቱ እየተደረገ ያለ እኩይ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በውጭ ያሉ ሀይሎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የኢትዮጵያን የእውነት መንገድና የፍትህ ጥያቄ በማዛባት ያለ የሌለ ርብርብ ከማድረጋቸውም በላይ የውስጥ ብጥብጦችን ዋነኛ የውጊያ አውድ አድርገው በስፋት እየተቀሳቀሱ ይገኛሉ” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
በአሁኑ ሰዓት የድሃ ሞት እና ጭፍጨፋ እንዲሁም ያልተረጋጋች ሃገር መፍጠር የእርካታ ምንጫቸውና መኖሪያቸው ያደረጉ ሀይሎችን ያለምህረት የመታገል እንዲሁም በየደረጃው ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን አስጠብቃ የምትዘልቅ እና በታችኛው ተፋሰስ ሃገሮች ዘንድ የሚንፀባረቁ ፍላጎቶችን በሰላም እና በድርድር የመፍታት አቋም እንደወትሮው ፀንቶ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም፣ በራሷ ሉዓላዊ ግዛት፣ በራሷ ሃብት የተፈጥሮ ፀጋዋን ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ማድረግ፣ የሌሎችንም ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የምታደርገውን የፍትሃዊነት እንቅስቃሴ በዘለለ ያልተገባ ጫና መፍጠር እና ለዘመናት የነበረው ኢፍትሃዊ ስርዓት እንዲቀጥል ማድረግ ተቀባይነት የለውም ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን “ከመነሻ ጀምሮ ገንዘባችሁን፣ ጊዜያችሁን፣ ጉልበታችሁን፣ ሃሳባችሁን እና ድምፃችሁን በመስጠት ፕሮጀክቱ ወደ ማገባደጃው ምዕራፍ እንዲሸጋገር ድጋፍ ላደረጋችሁ በሃገር ቤት እና በውጭ ዓለም ለምትኖሩ ወገኖቻችን በሙሉ ያለንን ታላቅ አክብሮት እና ምስጋና በብሄራዊ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ም/ቤት እና በራሴ ስም እየገለፅኩ፤ ሁሉንም ጫናዎች በመቋቋም የምናስበው ዓላማ እንዲሳካ፤ ውስጣዊ አንድነታችን የድሎቻችን ሁሉ ምንጭ ስለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል፡፡