አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በቼክ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ሃገራት ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

መጋቢት 24 /2013 (ዋልታ) – አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በቼክ ሪፐብሊክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራት ዳይሬክተር ኒኮል አዳምኮቫ ጋር ተወያዩ።

በጀርመን፣ በቼክ እና በስሎቫኪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ከሃላፊዋ ጋር በህዳሴ ግድብ፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ፣ በ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ እና በሁለትዮሽ ጉዳይ ላይ በበይነ መረብ ተወያይተዋል፡፡

የቼክ መንግስት ለኮቪድ19 በሽታ መከላከል እና ለመደበኛ የጤና አገልግሎት፣ ለኦክስጅን ማምረቻ፣ ለጽኑ ህሙማን መርጃ የሚውል 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ይፋ በማድረጉ አምባሳደር ሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ መንግስት በህወሓት ቡድን ላይ በወሰደው እርምጃ ቀጠናው የትርምስና የሽብርተኞች ማዕከል ከመሆን እንደተረፈ ገልጸው፣ በክልሉ እስከአሁን ለ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች የሰብአዊ ዕርዳታ ድጋፍ አስረድተዋል፡፡

ከተሰራጨው ዕርዳታ ውስጥ 70 በመቶ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ መሆኑን በመጠቆም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያበረከተውን 30 በመቶ ድርሻ እንዲያሳድግ ጥሪ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ እና የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብን በተመለከተ ዝርዝር ገለጻ በማድረግ ሁለቱም ጉዳዮች በድርድር ይፈቱ ዘንድ የኢትዮጵያ መንግስት ጽኑ አቋም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለጎረቤት ሃገራትም ጠቀሜታ ያለው መሆኑንና ከግድቡ ጋር ያሉ ትክክለኛ መረጃዎችን በተገቢው መረዳት አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

ኒኮል አዳምኮቫ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከስደተኞች ጋር ያለባትን ጫና በመገንዘብ በተመድ የስደተኞች ኮሚሽን በኩል 10 ሚሊየን የቼክ ክራውን ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

አያይዘውም የኦክስጅን ማምረቻ እና ሌሎች ለጤናው ዘርፍ የሚውል 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት እንደተፈረመ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።