የትህትና ጥግ

የትህትና ጥግ

(በአመለወርቅ መኳንንት)
———————
በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት እጅግ ከሚወደዱ እና ከሚናፈቁ ሐይማኖታዊ ወቅቶች አንዱ ሰሙነ ሕማማት ነው፡፡ በመሆኑም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለው አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት /የሕማማት ሳምንት/ በማለት ትዘክረዋለች።
ሕማማት የሚለው ቃል “ሐመ”፣ “ታመመ” ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው። ሰሙነ ሕማማት በላቲን Hebdomas Sancta or Hebdomas Maior፣ በግርክ ደግሞ Ἁγία καὶ Μεγάλη Ἑβδομάς, Hagia kai Megale Hebdomas (ታላቁ ሳምንት) ተብሎ ይጠራል፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ ደግሞ ሰሙነ ሕማማት ይባላል።
በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ሰኞ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም፣ እንዳይጠወለግ፣ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል የሚታሰብበት ቀን በመሆኑ አንጾሖተ ቤተ መቅደስ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ዕለትም የአይሁድ ካህናት አለቆችና ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ በመሰብሰብ ጌታችንን እንዴት እንደሚይዙት ለመማከር ክፉ ጉባኤያቸውን የጀመሩበት ቀን ነው፡፡
በቤተክርስቲያናችን ቀጣዩ ቀን ማክሰኞ ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡
ዕለተ ረቡዕ ምክረ አይሁድ በመባል ይጠራል ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነውና፡፡
ዕለተ ሐሙስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡
ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም ይጠራል ፡፡ ጌታችን በዚህ እለተ እናንተ ለወንድማችሁ እንዲሁ አድርጎ በማለት የደቀ መዛሙርቱን አግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም ከሕጽበት ሐሙስ በተጨማሪ፣ ምስጢር ሐሙስ፣ አረጓዴው ሐሙስ፣ ጸሎት ሐሙስ በመባል እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስረዳሉ፡፡
ይህ ቀን ዝቅ ብሎ ሌሎችን ከፍ ማድረግን፣ ትህትናን መከባበርን፣ ይቅርታና፣ ደግነትን የምንማርበት ለሌሎች መልካም መሆንን በተግባር ያየንበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ ይቅርታ ሰዎች እንዲለወጡ ዕድል የምንሰጥበትና እስከ ሞት ድረስ እንዲታመኑልን የሚያደርግ ታላቅ ድርጊት ነው። መውደቅ መጨረሻ ቢሆን ኖሮ ሰው ሰው ለመሆን ባልበቃ ነበር።
ይቅር አለማለት አንዱ በደል ነው ምክንያቱም እምነትና ይቅርታ የተያያዙ ነገሮች ናቸውና። ይቅርታ የምናደርገው ለማንም ብለን አይደለም ለራሳችን ሰላም ብለን ነው።
እግዚአብሔር አምላካችን የትላንት በደላችንን ቢያስብብን ኖሮ ማንም በሕይወት አይኖርም ነበር። ነገር ግን እኛ በሕይወት ዘመናችን ብዙ ጊዜ ይቅርታ ማድረግ አለመደብንም፡፡ እግዚአብሔር ግን በሕይወት ዘመናችን ሳይሆን በየዕለቱ ሁልጊዜ ይቅር ይለናል።
በመስቀል ላይ ራሱን አሳልፎ ለሰጠን ፈጣሪያችን ለከፈለልን ዋጋ መልሳችን፣ ውለታችን ምንድነው? እርስ በርስ መለያየት፣ በቋንቋ በብሔር፣ በዘር መከፋፈል ወይንስ አላፊና ጠፊ በሆነ ገንዘብ መገዳደል? ትተነው በምንሄደው መሬትና ድንበር መጠፋፋት? ግን ለምን?
እውነት እኛ የተቀደሰች፣ የተባረከችዋ ምድር የኢትዮጵያ ልጆች ነን? በተወለዱበት በኖሩበት ሀገር ወገኖቻችን በግፍ በጭካኔ እየቆሰሉ እየተገደሉ፣ እየተሰደዱ ይገኛሉ፡፡ እውነት ይህን ነው ከሐይማኖታችን የተማርነው?
በሀገራችን “ቂም ይዞ ፀሎት ሳል ይዞ ስርቆት” የሚለው አባባል መልዕክቱ እጅግ ጥልቅ ነው፡፡ እንዴት እርስ በእርስ እየተከፋፈልን፣ እየተገዳደልን ፆመኞች ነን፤ ሀይማኖተኞች ነን እንላለን? የማናችንም ሀይማኖት ይህንን አይፈቅድም፡፡ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ለሚፈጥነው እድሜያችን እንዴት ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ህይወት እንቀጥፋለን? አንድ ደቂቃ አይደለም አንድ ሰከንድ እንዴት በህይወት እንደምንኖር ዋስትና የሌለን በፈጣሪ እጅ የተያዝን ፍጡሮች ነን:: ነገር ግን ለማናውቀው ነገ ዛሬያችንን ለሀብት፣ ለዝና፣ ለስልጣን እንዲሁም ለሌሎች ጥቅሞች ስንል ግፈኞች ሆነናል፡፡ እውነት በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንድንኖር አልተፈጠርንም፡፡
በዕለተ ሐሙስ (ሕጽበተ ሐሙስ) ከእራትና ከቁርባን በኋላ አመሻሽ ላይ አይሁድ ሰይፍና ጎመድ ይዘው ወንበዴ፣ ሽፍታና ቀማኛ እንደሚይዙ ሁሉ ንጹሁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመያዝ መጡ እርሱም በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ ሰጣቸው ያዙትም ከዛም እስከ አርብ ስድስት ሰዓት ሲያንገላቱት ሲያሰቃዩት ቆይተው ከብዙ እንግልትና መከራ በኋላ ሰቀሉት፡፡ ጌታችንም “የሚያደርገቱትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ቅድስት ነፍሱን በፈቃዱ ከቅዱስ ስጋው ለየ እናም የቀን ጨለማ በምድር ላይ ሁሉ ሆነ የቤተመቅደስ መጋረጃም ከላይ ወደ ታች ተቀደደ፡፡
የሰሙነ ሕማማት ቅዳሜ፣ “ሰንበት ዓባይ” ትባላለች፤ ጌታችን የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ፈጽሞ በከርሠ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት ናት፡፡ ሁለተኛም፣ ይህች ዕለት ሥዑር ቅዳሜ፤ የተሻረች ቀዳሚት ሰንበት ትባላለች፡፡ ሥዑር መባሏ በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ነው፡፡
በመጨረሻም ትንሳኤ ማለት ተንሥአ ካለው የግዕዝ ግሥ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም መነሣት አነሣሥ ማለት ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ በስሙ ላመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ታላቅ ትንሣኤ ነው፡፡ ምክንያቱም በእርሱ ትንሣኤ ታላቅ ጸጋ አግኝተናል።
በትንሣኤው ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል። ምድራዊያን የነበርን ሰማያዊያን፣ ሙታን የነበርን ሕያዋን፣ ሥጋዊያን የነበርን መንፈሳዊያን ሆነናል፡፡ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የተመለስንበት መንፈሳዊ የነጻነት በዓል ነው፡፡ ክርስቶስ ለሙታን ሁሉ በኲር ሆኖ ተነሥቶአል፡፡
የሙታንን ሁሉ መነሣት የሚያረጋግጥልን የጌታ ትንሣኤ ነው፡፡ የክርስቶስም ትንሣኤ መርገመ ሥጋ ፣መርገመ ነፍስ፤ ሞተ ሥጋ ፣ሞተ ነፍስ የተሻረበት ርደተ ገሃነም ጠፍቶ፣ በአዳም የተፈረደው ፍርድ ሁሉ ተደምስሶ፤ ፍጹም ነፃነት፣ የማይለወጥ ደስታ፣ የተገኘበት ስለሆነ ፋሲካ ይባላል፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ እግዚአብሔር እኛን ምን ያህል እንደ ወደደን የምናስተውልበት፣ የፍቅሩን ጥልቀት፤ የቸርነቱን ስፋት የምናደንቅበት፤ የነፍሳችን የዕረፍት ቀን ነው፡፡
እናም የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል ስናከብር ፤ በእርሱ ላይ ያለንን እምነትና በእርሱም መታመናችንን በማጽናት፣ በእምነትና መልካም ምግባር በመከተል እንዲሁም እርስ በእርሰ በመተሳሰብ እና ለሀገራችን ሰላም እና እድገት የጋራ ሀላፊነታችን በመወጣት፣ በፍቅር፣ ይቅር በመባባል እንዲሁም በመቻቻል በዓለ ትንሳኤውን ልናከብር ይገባል፡፡
የመሸ ቢመስልም፣ ንጋቱ ቅርብ ነው።
የኢትዮጵያችንን ትንሳዔ ለማየት ያብቃን!
ቸር ይግጠመን!