የትንሣዔ በዓል በመተሳሰብ እንዲከበር የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጠየቁ

ሚያዝያ 23/2013 (ዋልታ) – የትንሣኤ በዓል በመተሳሰብ እንዲከበር የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የደቡብ እና የሲዳማ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት ትንሳኤ አሁን ላይ እንደ ሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች ለማለፍ ምሳሌ ይሆነናል ብለዋል።

አሁን ላይ የገጠሙንን ፈተናዎች አልፈን የምንሻገር እንድንሆን ተስፋን የምንሰንቀበት በዓል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን በዓል ሰናከብር ግን ከኮሮና ቫይረስ ራሳችንን መጠበቅ ይገባናል ነው ያሉት።

በዚህ በዓል ላይ እንደተለመደው ሁሉ እርስ በእርስ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ማክበር ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋል።

ትንሳኤ ለሰው ልጆች ሁሉ ከመከራ የመነሳት የተስፋ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ እኛም አሁን የገጠሙንን የውስጥና የውጭ ችግሮች ተቋቁመን ፈተናዎችን በፅናት ለመሻገር መነሳት ይኖርብናል ሲሉ ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል ሲከበር በየአካባቢው በተከሰቱ ማንነት ተኮር ጥቃቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ምዕመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን እና ፍቅርን መማር ይገባቸዋል ብለዋል።

ም/ርዕሰ መስተዳድሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሠው ልጆች ሲል ብዙ መከራ ተቀብሎ ይቅርታ እና ፍቅርን ያስተማረበት በዓል በመሆኑ ምዕመናን በዚህ ተምሳሌት መተሳሰብ እና በጎ ተግባርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በተመሳሳይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የትንሳኤ በአልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በሀገራችን እያየን ያለነው ጥላቻ እና መገፋፋት የክርስቲያኖች መለያ አይደለም ያሉ ሲሆን ይህን ታሳቢ በማድረግ በትንሣኤ በዓል ፍቅርን እና አንድነትን በመስበክ ማክበር ይገባል ብለዋል።

በዓሉን በማክበር ሂደት ውስጥ እራሳችንን ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ በማያደርገን ሁኔታ ማክበር ይገባናልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ።

ዘገባው የኦቢኤን ነው።