ኅዳር 16/2015 (ዋልታ) የትግራይ ክልል ህዝብ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል ሲሉ የአክሱም፣ አደዋና ሽሬ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ለሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚነት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡
በመንግስትና ህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ተስፋ የሰነቀ ነው፡፡
በዚህም የመማር ህልማቸው የተቋረጠባቸው ወጣቶች የተሻለ ነገን ማለም ጀምረዋል፣ ጦርነት በሚሉት ሰው ሰራሽ ጠላት የልጆቻቸውን ወጥቶ መመለስ ለሚጠባበቁ እናቶችም እፎይታ ተፈጥሯል፡፡
በትግራይ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎችም በሰላም ስምምነቱ እጅግ መደሰታቸው ገልጸው፤ ለተግባራዊነቱ ሁሉም በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሽሬ፣ አክሱምና አደዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ የሰላም ስምምነቱ መላ ኢትዮጵያዊያንን ባለ ድል ያደረገ ነው፡፡
በጦርነቱ ህይወት ተገብሯል፣ ሃብትና ንብረት ወድሟል፤ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ችግር ሊደርስባት አይገባም ብለዋል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ወንድማማቾች ነን፤ ችግሮቻችንን በሰላም በመፍታት አንድ መሆናችንን የምናሳይበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የትግራይ ህዝብ ጦርነት ሰልችቶታል የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ በሰላም ስምምነቱ መላ ኢትዮጵያውያን አትራፊዎች ነን ብለዋል።
በመሆኑም ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ወደ መደበኛ ኑሯችን እንድንመለስ ሁሉም ዜጋ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡