ነዳጅን በወርቅ ለመግዛት ማቀዷን ጋና አስታወቀች

ኅዳር 16/2015 (ዋልታ) ጋና ከውጭ የምትገዛውን ነዳጅ እና የነዳጅ ምርቶች ከዶላር ይልቅ በወርቅ ለመግዛት ማቀዷ ተሰምቷል፡፡የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ (ሴዲ) ከዶላር ምንዛሬ አንጻር መዳከሙ እና ሀገሪቱ ያላት የዶላር ምንዛሪ ክምችት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው ሀገሪቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው፡፡ምክትል ፕሬዝዳንት ማሃሙዱ ባውሚያ፤ አዲሱ እቅድ የክፍያ ሚዛናችንን በመሰረታዊነት ከማስተካከሉም ባሻገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የሚገኘውን የሀገሪቱ ገንዘብ ምንዛሬ ዋጋ ያረጋጋዋል ብለዋል፡፡በተጨማሪም የሀገሪቱ የምንዛሬ ክምችት በፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ ላይ 9 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን ይህ አኃዝ በ2022 መስከረም ላይ ወደ 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን መውረዱ ለአዲሱ እቅድ አነሳስቷታል፡፡እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገለጻ የነዳጅ ግብይቱን በወርቅ መፈጸም፤ የምንዛሪ ገንዘቡ በነዳጅ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንዳይኖረው ከማድረጉም በላይ በነዳጅ ንግድ ላይ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ ሻጮች ነዳጅ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ የማግኘት ግዴታ ውስጥ እንዳይገቡ ያደርጋቸዋል፡፡አዲሱ የጋና እቅድ በቀጣዩ አመት መጀመሪያ ላይ ይፋ እንደሚደረግ ሮይተርስን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡