የቻይና ኩባንያ በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቡና ማቀነባበር ዘርፍ ለመሰማራት ተስማማ

ነሐሴ 3/2015 (አዲስ ዋልታ) ሲ.ሲ.ኢ.ሲ.ሲ (CCECC) የተባለ የቻይና ኩባንያ ለእርሻ ውጤቶች ማቀነባበሪያ ምቹ ሆኖ በተገነባው ጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቡና ማቀነባበር ዘርፍ ለመሰማራት በዛሬው እለት የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈራረሙ ተገለጸ።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚ ሽፈራው ሰለሞን እንዲሁም ከሲ.ሲ.ኢ.ሲ.ሲ በኩል የኩባንያ ተወካዮች ስምምነት መፈራረማቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ አመላክቷል።

ኩባንያው ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ምቹ ሆኖ በተገነባው በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢንቨስት በማድረግ በጅማ እና በአካባቢው በስፋት የሚገኘውን የቡና ምርት ማቀነባበር እና እሴት በመጨመር ስራ ላይ እንደሚሰማራ ተገልጿል።

ከፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ባሻገር በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዝዩአን፣ ኮሚሽነር ለሊሴ ነሚ እና አክሊሉ ታደሰ በኢንዱስትሪ ፓርኩ አረንጓዴ አሻራ ማኖራቸውም ተጠቅሷል።