የቻይና ኮሚኒስት እና ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲዎች ለብልጽግና ፓርቲ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላለፉ

መጋቢት 3/2014 (ዋልታ) የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ እና የሩሲያው ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ትናንት አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ለጀመረው ብልፅግና ፓርቲ የተሳካ ጉባኤን በመመኘት ምልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ለሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ እንኳን ደስ አላችሁ ሲል የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቱን አስተላልፏል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በመልዕክቱ ከብልጽግና ጋር ላለው ወዳጅነት ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጥ በመግለጽ ግንኙነቱንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

የሁለቱ ፓርቲዎች መደጋገፍ ለአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትና እና ሁሉን ዐቀፍ ለሆነው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት መጎልበት የሚኖረው አስተዋጽኦ ላቅ ያለ በመሆኑ ለአገራቱ ሕዝቦች ደኅንነትና ተጠቃሚነት ጠንክሮ እንደሚሰራ አስታውቋል።

የሁለቱ ፓርቲዎች፣ አገራት እና ሕዝቦች ወዳጅነት ዘላቂ እንደሚሆንም ያለውን እምነት በመግለጫው አመልክቷል።

በተመሳሳይ ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ለብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ በላከው መልዕክት በጉባኤው ኢትዮጵያዊያንን የሚጠቅም ወሳኝ እና ጠቃሚ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት እምነቱ መሆኑን አስታውቋል።

ሁለቱ ፓርቲዎች ወዳጅ ፓርቲ መሆናቸውን ያነሳው መልዕክቱ ይህም ወዳጅነት በፓርቲዎቹ መካከል በተገቡ የትብብር ስምምነቶች የጠነከረም እንደሆነ አመላክቷል፡፡

የሁለቱ ፓርቲዎች ትብብር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ በመስራቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቱን የገለጸው የዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ሩሲያ በአፍሪካ ኢትዮጵያን አስተማማኝ አጋር አገር አድርጋ እንደምትወስድ በመጠቆም ሀገራቱ በዓለም ዐቀፍ ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት ወይም የሚመሳሰል አቋም ማንፀባረቃቸው የዚህ ማሳያ ነው ብሏል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW