ግንቦት 12/2013 (ዋልታ) – የንባብ ባህልን በሀረሪ ክልል ለማዳበር የንባብ ሳምንት በሀረር ከተማ ተጀምሯል፡፡
የንባብ ሳምንቱ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ ከሀረሪ ክልል ቱሪዝም፣ ባህል እና ቅርስ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡
የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙክታር ሳሊ የንባብ ሳምንቱ ከሸዋል ኢድ በዓል ጋር ተያይዞ መጀመሩ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸው፣ የመጽሐፍት ክበባት በትምህርት ቤቶች መቋቋሙ ተማሪዎች ለንባብ ትኩረት እንዲሰጡ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ ተወካይ ሙስጠፋ ዑስማን በሀረር ከተማ የተጀመረው የንባብ ሳምንት በቀጣይም ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራበታል ብለዋል፡፡
አክለውም “መጽሐፍት ለዕውቀት ገበታ፤ መዛግብት ለዘመን ትውስታ” በሚል መርህ የተጀመረው የንባብ ሳምንት ከሀረሪ ክልል በተጨማሪ በሌሎች ክልሎችም እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
(በቁምነገር አህመድ)