ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ክልሉ ሕግ የማስከበር ሙሉ አቅም እንዳለው ገለጹ፡፡
ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ወያኔና የወያኔ ፈረሶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው ብለዋል።
በግንባር አካባቢ የወያኔ ፈረስ ሆነው የሚያገለግሉትን ኃይል አዘጋጅተን እየተፋለምን ነው ሲሉም አክለዋል።
የአማራ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት በዝርዝር አጥንቶ ክልሉን ለማዳከም የሚሠሩ ጠላቶች መኖራቸውን አረጋግጧል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የውስጥ ጠላቶችን ለመዋጋት የውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ብለዋል፡፡
የኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ የመግባት እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ እየወደቀ መሆኑንም ተናግረው ውስጡን እያዳከመና እየከፋፈለ የሚገኝ ኃይል እንዳለም አረጋግጠናል ነው ያሉት።
ሕገወጥ ተኩስ በአጭር ካልተቀጨ በስተቀር ለኅብረተሰቡ ስጋት ይሆና ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የልማት እንቅስቃሴዎች በሰላማዊ ሁኔታ እንዳይከናወኑ እየተደረገ መሆኑን መገንዘባቸውንም ተናግረዋል።
የኮንትሮባንድ ንግድ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸው አንዳንዱ ሕገ ወጥ ንግድ በጦር መሳሪያ ጭምር እየታገዘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በታጠቁ ኃይሎች ምክንያት የመንግሥት አቅጣጫዎች እንዳይተገበሩ የሚያደርጉ መፈጠራቸውንም ተናግረዋል።
ሃይማኖትን ሰበብ በማድረግ እርስ በርስ በማጋደል ክልሉ የፀጥታ ስጋት ውስጥ እንዲቆይ የሚያደርጉ ሁኔታዎች መገኘታቸውን አመላክተዋል። ይህም ለውጭ ጠላት ተገላጭ እንዲሆን እያደረገ መሆኑንም መገምገማቸውንም ጠቁመዋል።
በየደረጃው ያለ አመራር እየተሳተፈበት የሕግ ማስከበር ሥራው እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀው እየተወሰደ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ ጅማሮው አበረታች መሆኑንም አንስተዋል።
ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን በማስለቀቅ እና ሕጋዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። የሕግ ማስከበር ሥራው አስፈላጊና ስኬታማ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ሕግ የማስከበር ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል። የአማራን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እንሠራለን ነው ያሉት።
ሕግ የማስከበሩ ሥራ የመንግሥትን ኃላፊነት የሚያረጋግጥ እና ሕዝብን የመታደግ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ወጣቶች ከመንግሥት ጋር በመሆን ለሕግ ማስከበሩ ሥራ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ተጠርጣሪዎችን እየያዙና በውይይት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም አንስተዋል።
ያለ አግባብ የተያዙ ሰዎች ካሉ አጣሪ ኮሚቴው እያጣራ አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጣልም ነው ያሉት። ጥፋተኞች ግን በሕግ አግባብ ሊቀጡ ይገባል ነው ያሉት።
ከክልሉ ውጭ ተይዘው ጠፉ የሚባሉት ትክክል አይደለም መስተካከል አለበትም ፤ የተፈጠረ ስህተት ካለም መታረም አለበት ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ሙሉ አቅም አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሕገ ወጦችንና ሥርዓት አልበኞችን የመቆጣጠር አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር ሥራ ኅብረተሰቡ ከአሉባልታ ተቆጥቦ በጥንቃቄ እንዲመረምረውም አሳስበዋል።
የጦር ነጋሪት እየጎሰመ ያለውን ጠላት በመከላከያ ሠራዊት፣ በልዩ ኃይል፣ በሚሊሻና በፋኖ ሕዝባችን ደጀን አድርገን እንመክታለን ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡