ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) – የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ክልሉ ከህወሓት የሽብር ቡድን የሚፈፀምበትን ትንኮሳ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የገለፁት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ ነው።
በመግለጫቸው በትግራይ ውስጥ ያለውና በፌደራል መንግሥት የተወሰነው ውሳኔ ከአማራ ክልል አንጻር ያለውን አንድመታ በማቀድ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሀገር እንድትሆን እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ዋጋውን ያገኘበት የሕግ ማስከበር ዘመቻ መከናወኑን የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ ለሀገሪቱ ስጋት የሚሆንበት ደረጃ ላይ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡
መከላከያው ከትግራይ ሲወጣ ለላቀ ግዳጅ ራሱን ለማዘጋጄት መሆኑን እንደሚረዱም ተናግረዋል፡፡
የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔው የትግራይ ሕዝብ ወደ ልማት እንዲገባ እድል የሚሰጥ ነውም ብለዋል፡፡ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የሚጠበቅ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ የአማራን ሕዝብ የቻለውን ሁሉ አድርጎ በድሎታል፣ ቡድኑ ጸረ አማራ መሆኑን በግልጽ አውጥቶታል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ሕዝብና መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ሂሳብ አያወራርድም፣ የትግራይ ሕዝብ ጠላታችን አይደለም፣ ትህነግ ግን ጠላታችን ነው፣ ማናቸውንም ነገር ለማድረግ ወደኋላ እንደማይል እናውቃለን፣ ከዚሕ አንጻር ለሚመጣው ሁሉ የአማራ ሕዝብ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ንቀት የተመላበት እብሪት እያሳየ እንደሆነ የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ በአማራ ሕዝብ ላይ አወራርዳለሁ የሚል ካለ እንጠብቀዋለንም ብለዋል፡፡
የአሸባሪው ትህነግ ዋነኛ ዓላማ የትግራይ ሕዝብን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር መነጠል መሆኑንም አንስተው የአማራ ሕዝብ ለማንኛውም ነገር በሥነልቦና ዝግጁ ነውም ብለዋል፡፡
ወልቃይት ጠገዴና ራያ የማን እንደሆኑ የታወቀ ነው፣ ቦታዎቹ የተወሰዱት በማጭበርበርና በጉልበት ነው፣ ለማንነት ጥያቄው ሕዝብ ዋጋ ከፍሏል፣ አካባቢዎቹ የአማራ ግዛት ናቸው፣ በአማራ ክልል ሥር እያስተዳደርናቸው ነው፣ ወልቃይት ጠገዴንና ራያን እንወስዳለን ማለት የማይታሰብ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በአካባቢዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ የሚንቀሳቀሰው ቀልድ ነው፣ አይሳካለትም፣ ዋጋ ያስከፍላል ነው ያሉት፡፡
አሸባሪ ትህነግ በአማራና በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሽብር ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ ባለፉት ዓመታትም ጥፋት ሲፈጽም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ዓለም አሸባሪው ትህነግ የሚፈፅመውን ወንጄል እየተመለከተ ወንጀሎችን አጉልቶ አለማውጣቱ ፍትሕ አለመኖሩን የሚሳይ ስለመሆኑም መግለጻቸውን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡
ማይካድራ ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በዓለም አቀፉ የመገናኛ አውታሮች ጎልቶ ሲወጣ አይታይም፣ ፍጹም ፍትሓዊነት የጎደለው የሚዲያ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሚዛን እንደሚያሳዝናቸውም ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እውነታውን እንዲዘግቡ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ዓለማቀፋዊ ማኅበረሰብ እውነቱን በማወቅ ለሰላም እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዲያስፖራው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለችበትን አሁናዊ ሁኔታ በመረዳት ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን እንዲቆምም ጠይቀዋል፡፡ ትህነግ ሀገር ሰላም እንዳይሆን እየሠራ መሆኑን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው ከመንግሥት ጎን መቆም አለባቸው ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ትህነግ የሁሉም ጠላት መሆኑን አውቀው አደብ እንዲገዛ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበው ትህነግ ሥርዓት ካልያዘ ሀገርን መልሶ እንደሚያተራምስም ተናግረዋል፡፡
ሂሳብ ሲወራረድ ቆመን ማዬት ስለሌለብን ለማንኛውም የትግል ጥሪ የአማራ ወጣቶች ዝግጁ መሆን አለባቸውም ብለዋል፡፡ ትህነግ አማራን ሊያጠቃ እየተንቀሳቀሰ ያለ ጠላት ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ እንደ አመጣጡ ለመመለስ በሚደረገው ጥሪ ሁሉም እንዲዘጋጅ ነው የጠየቁት፡፡
የማኅበራዊ አንቂዎች ትክክለኛውን መረጃ በመያዝ እንዲሰሩና በተሳሳተ መረጃ የተሳሳተ ታሪክ እንዳይሰሩም አሳስበዋል፡፡
አሁን ላይ የፖለቲካ ልዩነት ጉዳይ አይደለም ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግሥት ጠላትን ለመመከት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ እንዲሠሩም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ የጸጥታ ኃይል የትህነግ አሸባሪ ቡድን የሚደርገውን ጥቃት በአግባቡ እንደሚያስተናግደውም እርግጠኞች ነን ብለዋል፡፡
ሕዝቡም በተልእኮ ላይ ያሉ የጸጥታ አካላትን ቤተሰቦች በማገዝ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡ ኢኮኖሚን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ማኅበረሰቡ አንድም ቀን ከሥራው ወደኋላ እንዳይልም አሳስበዋል፡፡