የአሜሪካው ሴናተር ጂም ኢንሆፌን በኢትዮጵያ ውጤታማ ጉብኝት ነበራቸው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – የአሜሪካው ሴናተር ጂም ኢንሆፌን በኢትዮጵያ ውጤታማ ጉብኝት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቱ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ዓበይት የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ክንውኖችን አንስተዋል።

ከዚህም መካከል የኢትዮጵያና አሜሪካን ጉዳይ በተመለከተ ሴናተር ኢንሆፌን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በሰፊው መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲሻክር እንደማትፈልግ ገልጸው፣ “በጋራ ወዳጆች አማካኝነት ወደነበረበት እንዲመለስ እየሰራን ነው” ብለዋል።

በአንዳንድ ስሜታዊ በሆኑ ሰዎች የሚራመዱና የሚንፀባረቁ አስተያየቶች የግለሰቦች እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቋም እንዳልሆኑ እንዲታወቁም አስገንዝበዋል።

“ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ከማንኛውም አገር ጋር ጠንካራ ግንኙነት ማጠናከር ነው የምትፈልገው፣ የወዳጅነት ወሰንም የለም” ሲሉ አክለዋል።

በሌላ በኩል ባሳለፍነው ሳምንት 1 ሺህ 147 ኢትዮጵያዊያን ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በመግለጫቸው አንስተዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በዓለም በአቀፍ ስደተኞች ድርጅት መካከል ውይይት መደረጉንም ገልፀዋል።

በሳምንቱ 10 አገራት አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ያቀረቡ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴም በየአገራቱ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩንና ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ እንዳስረዷቸው ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ደመቀ መኮንንም ከሞሮኮ አቻቸው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ያመለከቱት ቃልአቀባዩ፣ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ብሎም ከዚህ በፊት የተደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑም መነጋገራቸውን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከተለያዩ አገራት ጋር የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተግባራት ተከናውነዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በኢትዮጵያ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነት የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎችም በውጭ አገራት ለአብትም በኖርዌይ፣ ካናዳ እና ኢጣልያ መካሄዳቸውንም አስታውሰዋል።