“የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ማራመድ ይገባል”- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

በኢትዮጵያ የቆየውን የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ማራመድ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ተናገሩ።

የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ችቦ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ጋምቤላ ክልል ሲገባ አቀባበል ተደርጎለታል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፣ የሕወሓት ጁንታ ሲያራምደው የነበረውን የከፋፋይ አስተሳሰብ በማስወገድ አንድነትንና አብሮነትን የመገንባቱ ተግባር ሊጠናከር ይገባል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን በማጠናከር የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ እና የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ማራመድ እንዳለለባቸውም ተናግረዋል።

የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ችቦ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በቅብብሎሽ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እንዲከበር የተወሰነው በሕዝቦች መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን አንድነት እና ወንድማማችነት ለማጠናከር መሆኑን አቶ ኡሞድ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሸዋል ንጉሴ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ችቦውን ለጋምቤላ ክልል ሲያስረክቡ “ኢትዮጵያ ለሁሉም የምትበቃ ቤታችን፣ ከለላ እናታችን ናት” ብለዋል።

በሀገሪቱ ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና  እንዲረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እና በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  በዓል ጁንታው ሀገር ለማፍረስ የከፈተው ዘመቻ በተቀለበሰበት ማግስት እየተከበረ መሆኑ የተለየ እንደሚያደረግው ጠቅሰዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ አቶ ጁል ናጋል በበኩላቸው ባለፉት 27 ዓመታት ህዝቦችን ለመለያየት ሲሰበክ የነበረውን ከፋፋይ አስተሳሰብ በማስወገድና አንድነትን በማጠናከር የተጀመረው ልማት ለማስቀጠል በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

በሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ጭምር ታጅቦ ትናንት ጋምቤላ ከተማ የደረሰው  የህብር ብሄራዊ አንድነት ችቦ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች  እና የአካባቢው ነዋሪዎች አቀባበል የተደረገ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።