የአውሮፓ ኅብረት የመንግሥትን መልካም ጥረቶች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

ግንቦት 6/2014 (ዋልታ) የአውሮፓ ኅብረት የመንግሥትን ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ ያሳለፈው የተኩስ አቁም ውሳኔ እና ለችግሮች እልባት ለመስጠት እየተጓዘበት ያለው መንገድ አበረታች መሆኑን ገልጾ ጥረቶቹ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛን አኔት ዌበር (ዶ/ር)ን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና በሰሜኑ ግጭት እና በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየተደረገ ስላለው ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ለልዩ መልዕክተኛዋ ገለጻ አድርገዋል።

መንግሥት ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጎ እርዳታ እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰብአዊ እርዳታ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሰብአዊ እርዳታ እያሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀትም ሀገራዊ የምከክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱ፣ ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ በጦርነቱ እና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እንዲዳረስ የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት አውጆ እየተጓዘ ነው፤ በግጭቱ የተፈጠሩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ለመመርመር እና ተጠያቂ ለማድረግ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሰራም ነው ብለዋል።

ግብረ ኃይሉም አሁን ላይ 100 ባለሙያዎችን እንዳሰማራ ተናግረው መንግሥት የተፈጠሩ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ወቅት ግን የሕወሓት የሽብር ቡድን ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

ይህ የሽብር ቡድን አሁን ላይ በሕዝብ ማዕበል ወደ ጦርነት ለመግባት የጥፋት ሴራውን እየነደፈ መሆኑን ገልጸው ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በሕወሓት የሽብር ቡድን ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳርፍ ይገባልም ነው ያሉት።

የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ  አኔት ዌበር (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግሥት ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ ያሳለፈው የተኩስ አቁም ውሳኔ እና ለችግሮች እልባት ለመስጠት እየተጓዘበት ያለው መንገድ አበረታች ነው ብለዋል።

ልዩ መልዕክተኛዋ የአውሮፓ ኅብረትም ለዚህ የመንግሥት መልካም ጥረቶች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ከልዩ መልዕክተኛዋ ጋር በወቅታዊው የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ እና በኅዳሴው ግድብ ዙሪያም ተወያይተዋል።

በኅዳሴው ግድብ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶች በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ በውይይት ይፈታሉ ብለን እናምናለን፤ ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም አላት ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት እና ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በግጭቱ እና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልምመጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።