የአየር ንብረት ለውጥ ከየትኛውም አገራት የበለጠ የሚጎዳው ታዳጊ ሀገሮችን ነው -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ሐምሌ 2፣ 2013 (ዋልታ) – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስፈልገዉን ገንዘብ ለማሰባሰብ  በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

መድረኩ የተዘጋጀው በባንግላዴሽ ጠቅላይ ሚኒስትር  ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስፈልገዉን ገንዘብ ለማሰባሰብ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በስብሰባው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ  የአየር ንብረት ለውጥ ከየትኛውም አገራት የበለጠ የሚጎዳው ታዳጊ ሀገሮችን መሆኑን እና የዘመኑ ዋነኛ ችግር ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡

ፕሬዝደንቷ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ  በጣም ተጋላጭ እንደመሆኗ መጠን በተለያዩ የጋራ እና ብሄራዊ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት የህብረተሰቡን የመቋቋም አቅም ለማሻሻል እርምጃ እየወሰደች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ያባባሰ መሆኑን ገልፀው ሁለቱም የተቀናጀ እና ፈጣን የጋራ እርምጃን እንደሚጠይቁ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ያደጉ አገራትም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የድርሻቸውን በተቻለ ፍጥነት እንዲወጡ መጠየቃቸውን ከፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።