የአደባባይ በዓላት ጎብኝዎች ቆይታ እንዲሳካ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል – የቱሪዝም ሚኒስቴር


መስከረም 5/2016 (አዲስ ዋልታ) የቱሪዝም ሚኒስቴር በመስከረም ወር በሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ላይ የሚታደሙ ጎብኝዎችን ቆይታ አስደሳችና የተሳካ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ፡፡

በሚኒስቴሩ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ፕሮሞሽን ዴስክ ኃላፊ ቢኒያም አስራት ለአዲስ ዲጂታል ዋልታ እንደተናገሩት በዚህ ወር ደመራ መስቀል እሬቻና የዓለም የቱሪዝም ቀን የሚከበሩበት ወር በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

የመስቀልና ደመራ እንዲሁም የኢሬቻ በዓል በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ከኃይማኖት ተቋማት በዘርፉ ከሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቱሪስቶችን ቆይታ አስደሳችና የተሳካ ለማድረግ ከሆቴል ባለቤቶች ከጸጥታ ተቋማት ከቱር ኦፕሬተሮችና ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በመወያየት የቅድመ ዝግጅቱ ስራ አየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመስከረም ወር የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚከበርና ኢትዮጵያም ቀኑን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው የቱሪዝም ቀን በዓለም ለ44ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ እንደሚከበር የጠቀሱት ሃላፊው “ቱሪዝምና አረንጓዴ ኢንቨስትመንት” በሚል መሪ ቃል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ አየተገበረች ካለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር የተገጣጠመ መሆኑን ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

የቱሪዝም ቀኑ በደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል የሚከበር ሲሆን በዕለቱ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚቀርቡና የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችም እንደሚጎበኙ ጠቁመዋል፡፡

አክለውም በዓሉ በአዲስ አበባም እንደሚከበርና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ለሶስት ሳምንት የሚቆይ አውደ ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኝዎች እንደሚከፈት ገልጸዋል፡፡

ከፊታችን በርካታ የአደባባይ በዓላት የሚካሄዱ በመሆኑ ኢትየጵያዊያን በነቂስ ወጥተው በበዓሉ ላይ እንዲሳተፉ ሀገራቸውን እንዲጎበኙ ሰላምን እንዲሰብኩና እንዲዝናኑ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ