የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተመራጭ አባላት ስልጠና

መስከረም 15/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተመራጭ አባላት በመልካም አስተዳደርና ሌሎች ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ተገለጸ።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ዘርፈሽዋል ንጉሴ ተመራጮች ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የከተማዋ ነዋሪ በመልካም አስተዳደርና ሌሎችም ችግሮች ውስጥ በመሆኑ ‘ትልቅ ስራ ይጠብቀናል’ ብለዋል።
በመሆኑም ተመራጭ የምክር ቤት አባላት የመሰረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎችም ስራዎችን በሕግ አግባብ በመከወን ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በስልጠናው የምክር ቤት አባላት የውስጥ አደረጃጀት፣ አሰራርና የስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 1/2000 እንዲሁም ደንብ ቁጥር 2 ሰነድ ላይ ገለጻ እየተደረገ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ የምክር ቤት ምስረታ የፊታችን ማክሰኞ መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡