የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በድርቅ ለተጎዱ ማህበረሰብ ድጋፍ አደረገ

ሚያዝያ 16/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ማህበረሰብ ክፍሎች የተለያየ ድጋፍ አደረገ።

የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ድጋፉ በመዲናዋ ከሚገኙ የትምህርት ማህበረሰብ የተሰበሰበ መሆኑን ገልጸው ልብስን ጨምሮ ምግብና የከብት መኖን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም 33 ሚሊየን የሚገመት ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

በችግራችን ወቅት እርስ በእርስ መደጋገፍ የቆየ ባህላችንና መገለጫችን ነው ያሉት ኃላፊው ይሄንኑ ታሳቢ በማድረግ ድጋፉን ላቀረቡ ለአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ማህበረሰብ ምስጋና እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ኤልዳና ሱሌማን በበኩላቸው በክልሉ በድርቅ የተጎዱትን ማህበረሰብ የመርዳትና መልሶ የማቋቋም ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው እስከ አሁን በተሰራ ስራም የብዙዎችን ህይወት መታደግ መቻሉን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮም ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው አሁንም እርዳታው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በታምራት ደለሊ