የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ”የክረምት ትጋት የዓመት ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል

 

ነሐሴ 13/2015 (አዲስ ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የሚያዘጋጀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ”የክረምት ትጋት የዓመት ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።

ወይይቱም በዋናነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

በመድረኩም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ዓለምጸሃይ ጳውሎስ፣ የአረንጓዴ አሻር መርሃ-ግብር ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፣ የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጸሚ ጀማል አህመድና የደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር ሰለሞን ክቤ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት ህዝብን በማስተባበር በርካታ አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ ስራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም በርካታ ዜጎች የአካባቢ ገጽታ በሚቀይሩ ስራዎች ላይ እየተሳተፉ መሆኑም ነው የተመላከተው።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ ለአብነትም በዘንድሮው ክረምት ብቻ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ20 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የተገኙ ለውጦች ህዝብን በማስተባበር በአጭር ጊዜ ኢትዮጵያን መለወጥ እንደሚቻል ትምህርት የሰጡ መሆናቸውም ነው በመድረኩ ተገልጿል፡