የአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በዘጠኝ ወራት 6 ሚለዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

ግንቦት 01/ 2013 (ዋልታ) – የአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ውጭ ከላካቸው ልዩ ልዩ ምርቶች 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።
የፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደርቤ ደበሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፓርኩ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ስራው ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሮበታል።
ይህም ሆኖ ግን አገሪቷ ከውጭ ምንዛሬ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንዳታጣና የፓርኩ ገቢ እንዳይቋረጥ ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ በፓርኩ ተመርተው ወደ ውጭ ከተላኩ ልዩ ልዩ ምርቶች 6 ሚለዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።
ፓርኩ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘቱ በተጨማሪ በስራ እድል ፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር ጉልህ አስተዋፆ ማበርከቱንም አቶ ደርቤ ተናግረዋል።
የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአሁኑ ወቅት ለ7 ሺህ ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ከነዚህም መካከል መሬታቸውን ለልማት አሳልፈው የሰጡ 360 አርሶ አደሮች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።
“ፓርኩ በአካባቢው ላለው ማህበረሰብ ማህበራዊ አገልግሎት አስተዋጾ በማድረግና ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።