ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የዛሬ ዓመት በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ በአሸባሪው ሕወሓት የተፈፀመውን ክህደት 1ኛ ዓመት መታሰቢያ ዝግጅት እያካሄዱ ነው፡፡
“ጠላትን እናጠፋለን ልማታቻንን እናስቀጥላለን” በሚል መሪ ቃል ነው እለቱን በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ሥነ ሥርአቶች እያከበሩ የሚገኙት፡፡
ኢትዮጵያ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቷን ተገንዝበናል ያሉት የከተማዋ ነዋሪዎች ኢትዮጵያ እንደምታሸንፍ ለዚህም አንድነታቸውን በማጠናከርና ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለፁት።
አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ አገርን ለማፍረስ የተነሱ ናቸው ያሉት ነዋሪዎች እነዚህን ቡድኖች የማጥፋት ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ነው ብለዋል።
እያንዳንዱ ነዋሪ አከባቢውን የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣትን በትኩረት እንዲተገብርም ተጠይቋል፡፡
አሸባሪዎቹን በመረጃ እና በገንዘብ የሚደግፉት በሕብረተሰቡ ውስጥ ተሰግስገዋል ያሉት የአዳማ ነዋሪዎች ለዚህም ነዋሪዎቹ ከፀጥታው ኃይል ጎን በመሰለፍ እንዲያጋልጡና አገራቸውን እንዲታደጉ ነው የጠየቁት፡፡
በሚልኪያስ አዱኛ (ከአዳማ)