የአፍሪካ-አሜሪካ ትብብር

መስከረም 5/2014 (ዋልታ) የቡና አምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚያስችል አዲስ የአፍሪካ-አሜሪካ ዲያስፖራ ኢኒሼቲቭ ይፋ ሆነ።
ኢኒሼቲቩ ቤኔፊት ኮርፖሬሽን ፎር አፍሪካ አሜሪካ የሚባል ሲሆን የአፍሪካና አሜሪካን ግንኙነት ከልመና ይልቅ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያስችል ነው ተብሏል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋና አረጋ ኢትዮጵያ ባላት የቡና ምርት ልክ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተጠቃሚ ባለመሆኗ ኢኒሼቲቩ ቡና አምራቹን አርሶ አደር ከመጥቀሙ ጎን ለጎን አገሪቱ በዓለም ዐቀፍ ገበያው ተወዳዳሪ እና ብቁ እንድትሆን ያስችላታል ብለዋል።
ለዚህም ስኬት ሚኒስቴሩ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ለ15 ዓመታት ይህን ኢኒሼቲቭ እውን እንዲሆን ሲሰሩ የነበሩት ጥበቡ አሰፋ በበኩላቸው አፍሪካ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግኑኝነት ከልመና ነፃ የሆነ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ታስቦ የተጀመረ በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
በመድረኩ በቡና ልማት ላይ የተሰማሩ የኅብረት ሥራ ኤጄንሲዎች ከብለስ ኮፊ አፍሪካ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የውል ስምምነት የፈረሙ ሲሆን፤ በአገሪቱ የሚገኙ 99 ሺሕ የኅብረት ሥራ ኤጀንሲዎች በኢኒሼቲቩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዑስማን ሱሩር ገልፀዋል።
ኢኒሼቲቩ በ3 የአሜሪካ ግዛቶች እንደሚጀምርም ተመላክቷል።
በድልአብ ለማ