የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር /አኖካ/ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአህጉሩን ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት አበረከተ

የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር /አኖካ/ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአህጉሩን ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት/ኦርደር ኦፍ ሜሪት/  አበረክቷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የስፖርትን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ መጠቀም የቻሉ መሪ ናቸው” ብለዋል።

ሽልማቱ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ለኦሎምፒክ ስፖርት ማደግ ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እውቅና የሚሰጥ ነው።

በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ይህንን ሽልማት ማግኘት ችለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ ስፖርት ያሳዩት ድጋፍና ለኦሎምፒክ መንደር ግንባታ ያደረጉት የ3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለሽልማት እንዳበቃቸው በሥነ ስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል።

ሽልማቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመወከል የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተቀብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስፖርት ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በሚገባ የሚጠቀሙ መሪ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም ስፖርትን በመጠቀም ላልተገባ ዓላማ ወደ ጽህፈት ቤታቸው ያመሩ የሠራዊት አባላትን ያረጋጉበትን ብልሃት አስታውሰዋል።

ይህን በማድረግም ኢትዮጵያን ይገጥማት ከነበረው ብጥብጥ መታደግ ችለዋል ነው ያሉት።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክት በሆነው የእንጦጦ ፓርክ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሰፊውን ቦታ እንዲዙ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ወጣቶች ለስፖርትና ለበጎ አድራጎት ተግባራት ትኩረት እንዲሰጡ አርዓያ በመሆን ጭምር ትልቅ ስራ ማከናወናቸውንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ቤራፍ በበኩላቸው በቆይታቸው ኢትዮጵያ እንግዳ በማስተናገድ የተካኑ ሕዝቦችን ያቀፈች ታላቅ ሀገር መሆኗን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቆይታቸው ለተደረገላቸው እንክብካቤም ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ በአዲስ አበባ ለተካሄደው የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ አበርክቶ ለነበራቸው ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።