የዋልታ ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ

“ደማችን ለመከላከያ ሰራዊታችን” በሚል መሪ ሐሳብ የዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ደም የመለገስ መርሃግብር አከናውነዋል፡፡

የሕወሓት የጥፋት ቡድንን ለማስወገድ እና ሕግ ለማስከበር መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊቱ የደም ልገሳው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በመገንዘብ ነው የደም ልገሳውን ያከናወኑት፡፡

በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት የዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ንጉሴ መሸሻ፣ ዋልታ ፈጣን፣ ተዓማኒ እና ወቅታዊ መረጃዎችን በማሰራጨት፣ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፋችንን በማሳየት በሀገራችን የተረጋጋ ሰላም ለመፍጠር ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡

የሀገር ሉአላዊነትን የሚነቅፍ ማንኛውንም ሃይል ለመመከት ለማህበረሰቡ አስተማማኝና ትክክለኛ መረጃን ተደራሽ በማደረግ ጠንከርን እየሰራን ነው ያሉት የተቋሙ ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ደም በመለገስ አጋርነታቸውን በማሳየታቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ህገወጡ የጥፋት ቡድን ላይ እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃን በተመከለተ ግንባር ድረስ በመገኘት በተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ መንገዶችን በመጠቀም መረጃዎችን ለማህበረሰቡ እያቀረበ ይገኛል፡፡