የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ዋና ጽሕፈት ቤት ህንፃ በቅርቡ ይመረቃል

የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ዋና ጽሕፈት ቤት

ጥር 1/2015 (ዋልታ) የኢዮጵያ እና ቻይና የግንባታ ሙያተኞች አሻራ ያረፈበት የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ዋና ጽሕፈት ቤት ህንፃ በቅርቡ ይመረቃል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተገነባው የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ዋና ጽሕፈት ቤት ህንፃ ማራኪ የህንጻ ጥበብ የታየበት ከመሆኑ በተጨማሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመጠናቀቅ ምሳሌ የሚሆን ህንፃ ነው ተብሏል፡፡

ዋና ጽሕፈት ቤቱ በ90 ሺሕ ሜትር ስኩዌር መሬት ስፋት ያለው ሲሆን የህንፃው ግንባታ ብቻ በ40 ሺሕ ሜትር ስኩዌር ላይ ያረፈ ነው፡፡

ህንፃው የድንገተኛ ህክምና ክፍል፣ የመረጃ ማዕከል፣ ላቦራቶሪ፣ የስልጠናና የስብሰባ አዳራሾችን እና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን የሚረዱ ማዕከላትን ያቀፈ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የዋና ጽሕፈት ቤቱ ህንፃ መገንባት የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ሚናን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግም ታምኖበታል፡፡

የህንፃው ግንባታ በቻይና መንግስት ድጋፍ የተከናወነ ሲሆን በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ችን ጋን በህንጻው ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ይታደማሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡