መስከረም 13/2016 (አዲስ ዋልታ) ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ በምክክር መፍትሄ በመሻት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የጋራ ኃላፊነታችን ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ላይ በማተኮር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለጋራ ሀገራችን የጋራ መፍትሄ የማበጀት ጉዳይ ለማንም የሚተው ሳይሆን የሁላችንንም ጥረትና ትብብር የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ገዥው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከ60 በላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም ከምንም በላይ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም አክለዋል።
የአገር ሉዓላዊነትንና ህልውናን የሚገዳደር ችግር ሲያጋጥም ጉዳቱ የሀገርና አጠቃላይ የህዝብ በመሆኑ ሁላችንም የመፍትሄው አካል ሆነን መገኘት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሰለጠነ የውይይት ባህልን በማዳበር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማጠናከር ይገባል ያሉት ሰብሳቢው የግጭት ምክንያቶችን በመለየትና በንግግር መፍትሄ በመሻት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁላችንም ዝግጁ መሆን አለብን በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በምንም አጋጣሚ የሚፈጠር ችግር መፍትሄ አለው የሚሉት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ በንግግርና በይቅርታ ቅራኔዎችን በመፍታት ብሄራዊ መግባባት መፍጠር አለብን ብለዋል።
በተለያዩ የዓለም አገራት የነበሩ ችግሮች በዘላቂነት የተፈቱት በመነጋገር በመሆኑ በኢትዮጵያም ችግሮች ሁሉ በኃይል ሳይሆን በውይይትና በንግግር ብቻ ሊፈቱ ይገባል ነው ያሉት።
በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።