የኢትዮጵያን ዲጂታል ሪፎርም ትግበራ ፕሮጀክት የሚያግዝ የ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዩሮ ስምምነት ተደረገ

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን መካከል የኢትዮጵያን ዲጂታል ሪፎርም ትግበራ ፕሮጀክት የሚያግዝ የ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዩሮ ስምምነት ተደረገ።

ስምምነቱን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር አብዮት ባዩ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ቡድን መሪ ሳነ ዊለምስ ተፈራመዋል።

ስምምነቱ የኢትዮጵያን የንግድ ስራ ቅልጥፍና ለማሻሻል የተነደፈውን ፕሮግራም የሚያግዝ ሲሆን፣ የዲጂታል ሪፎርም ፕሮጀክትን እንደሚደግፍም ተገልጿል።

ለዚህም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለአንድ አመት ለሚቆይ ፕሮጀክት የ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተነግሯል።

የገንዘብ ድጋፉ በድሬዳዋና በባህርዳር ከተሞች ብሔራዊ የንግድ ፖርታል ለመዘርጋት እንደሚውልም ተጠቁሟል።

ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በቀጣይ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ ሁኔታን ለማሻሻል እንዲሁም የመንግስትና የግል ዘርፍ ትብብርን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል፡፡