መስከረም 13/2014 (ዋልታ) “እጅ በመጠምዘዝ አሸባሪው ሕወሓትን ለመመለስ የሚደረግ የውጭ ጫና የኢትዮጵያዊያንን ድምጽ ካለማክበር የመነጨ ነው” ሲሉ የስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ።
ስድስተኛው አገር ዐቀፍ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተደረጉ ምርጫዎች በተለየ ሁኔታ ሰላማዊ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መከናወኑ ሲመሰከርለት ከርሟል።
ኢትዮጵያዊያን ያለማንም ቀስቃሽ ዝናብ፣ ፀሀይና ብርድ ሳይበግራቸው “ይሆነኛል” ያሉትን ፓርቲ በነጻነት መምረጣቸውም ሲገለፅ ነበር።
በምርጫው ከኢትዮጵያዊያን መንግሥት የመመስረት ይሁንታ ያገኘው የብልጽግና ፓርቲ ደግሞ በተያዘው መስከረም 24 ቀን 2014 አዲሱን መንግሥት ያዋቅራል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፓርቲያቸው በሚያዋቅረው አዲሱ መንግሥት ውስጥ በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተሳትፏቸው መጠን ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር ጀምሮ እስከ ሥራ አስፈፃሚ ድረስ በመንግሥት አደረጃጀት ውስጥ እንደሚካተቱ መግለጻቸውም አይዘነጋም።
በዛሬው እለትም በምርጫው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ያሸነፉ የፓርላማ አባላት የሕዝብ ተወካዮች ሚና፣ የአባላት ስነ ምግባር ደንብ እና በምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና ወስደዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አባላት እንዳሉት፤ ምዕራባዊያን የሕዝብ ይሁንታ ያገኘውን መንግሥት እጅ በመጠምዘዝ አሸባሪው ሕወሓትን ለመመለስ ጫና እያደረጉ ነው።
ይህም የኢትዮጵያዊያንን ድምጽ ካለማክበር የመነጨ አካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥረቱም ፈጽሞ ሊሳካ እንደማይችል ተናግረዋል።
ዲማ ነጋዎ (ዶ/ር) “ምዕራባዊያን በየመን ካለው አስከፊ ቀውስ ይልቅ ስለ ኢትዮጵያ አብዝተው ይጨነቃሉ ይህም ከሰብኣዊነት ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ እንደሚያሳድዱ ያሳያል” ብለዋል።
“አሸባሪው ሕወሓት መስዋዕትነት በተከፈለበት ትግል ከኢትዮጵያዊያን ጫንቃ ላይመለስ ተወርውሯል” ያሉት ዲማ፤ ምዕራባዊያን ይህን ጨቋኝ ቡድን መልሶ በኢትዮጵያዊያን ትክሻ ላይ ለመጫን የሚደረጉት ጫና ተቀባይነት የሌለውና የማይሳካ ሙከራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው፤ “የኢትዮዮጵያ ሕግ የሕወሓትን ቡድን በአሸባሪነት ፈርጇል፤ ይህም ትክክለኛና አግባብነት ያለው ውሳኔ ነው” ብለዋል።
በመሆኑም አሸባሪውን ቡድን ለመመለስ የሚደረግ የውጭ ጫና በራሱ ሽብርተኝነትን ማበረታታት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምዕራባዊያን አሸባሪ ብለው ከፈረጇቸው ቡድኖች ጋር ፈጽሞ እንደማይደራደሩ ሁሉ፤ “ኢትዮጵያንም በዚህ ልክ ሊገነዘቧት ይገባል ነው” ያሉት።
በተለይ “ለሰብኣዊ መብትና ዴሞክራሲ ተቆርቋሪ ነን ከሚሉ አገሮች ይህን አንጠብቅም” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወዳጅ ምዕራባዊያን አገራት ቢችሉ ሊያግዙን ካልሆነ ደግሞ “ሉዓላዊነታችንን ሊያከብሩ ይገባል ነው” ያለት።
“ኢትዮጵያዊያን በድምጻቸው የሚበጃቸውን መርጠዋል፤ ይህንን ውሳኔ የትኛውም አካል ሊያከብረው ይገባል” ያሉት ደግሞ ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) ናቸው።
በመሆኑም አሸባሪውን ቡድን ለመመለስ የሚደረግ የውጭ ጫና የኢትዮጵያዊያንን ድምጽ ካለማክበር የመነጨ መሆኑን እርሳቸውም ይስማማሉ።
ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር አሸባሪ ቡድኑን እስከወዲያኛው ላይመለስ መቅበር እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ሙስሊማ ረሸድ፤ ምዕራባዊያን ከእናንተ ይልቅ እኛ እናውቅላችኋላን ወደ ሚል ያልተገባ ጫና መግባታቸውን አንስተዋል።
ኢትዮዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ላይ ምን እንደሚከናወን ነቅተው እየተከታታሉ መሆኑን ገልጸው ከዚህ አኳያ “የምዕራባዊያን ጫና ፈጽሞ ሊሳካ አይችልም” ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን እየጨፈጨፈ ካለው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ይልቅ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር እየተከተለ ባለው የተዛባ አካሄድ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።