የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚዛን አማን 24ኛ ቅርንጫፉን አስመረቀ

ሚያዝያ 19/2013(ዋልታ) – የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተደራሽነቱንና የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት በሚዛን አማን ከተማ 24ኛ ቅርንጫፉን ዛሬ አስመርቆ ከፍቷል።

የገበያ ማእከሉን አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ድኤታ አቶ አንተነህ ፍቃዱ እና እንዲሁም በደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በይፋ ተከፍቷል።

የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር፣ ሚዛን አማን ቅርንጫፍ መገልገያ የሚሆን አርባ ሺህ ኩንታል የሚይዝ መጋዘንና ቢሮ ማዘጋጀቱም ነው የተገለፀው።

በቅርንጫፉ በዞኑ ለሚገኙ ስምንት ወረዳዎችና በምዕራብ ኦሞ ዞን ለሚገኙ ሰባት ወረዳዎች አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል የተባለ ሲሆን ቅርንጫፉ የምርት ጥራት መመርመሪያ ላቦራቶሪና የተሟላ የቢሮ አደረጃጀት አለው ተብሏል።

በህዝብ ጥያቄ የተከፈተው ቅርንጫፉ በሁለቱ ዞኖች የሚገኙ አርሶአደሮችና አቅራቢዎች ቡናቸውን በአቅራቢያ ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ለመውሰድ የሚያደርጉትን ተጨማሪ ጉዞ በአማካይ በ120 ኪሎ ሜትር እንሚቀንስም ተገልጿል።

አከባቢው ቡና ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ግንባር ቀደሙ በመሆኑ የቅርንጫፉ መከፈት ጥራት ያለው ምርት ተመርቶ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።

አካባቢው ሰሊጥ፣ አረንጓዴ ማሾ፣ ቅመማ ቅመምና ሌሎችም የግብርና ምርቶች የሚመረቱበት በመሆኑ ቅርንጫፉ እነዚህንም ተቀብሎ ለማስተናገድ ይችላል ሲል  የኢትዮጵያ ምርት ገበያ  ኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዘግቧል።