የሕወሃት ሕገ-ወጥ ቡድን ከ6.7 ቢሊዮን ብር በላይ ለወንጀል መፈጸሚያነት ማዋል እንዳይችል ተደርጓል፡- የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

ሚያዝያ 19/2013 (ዋልታ) – የሕወሃት ሕገ-ወጥ ቡድን ከ6.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነን ገንዘብ ለወንጀል መፈጸሚያነት ማዋል እንዳይችልና በሕገ-ወጥ መንገድ እንዳያሸሽ መከላከል መቻሉን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ቡድኑ ታሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ ባከናወነው የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ ሀብቱን ከጥፋት ለመከላከል መቻሉን ነው ያስታወቀው።

መጠኑ 97.5 ሚሊዮን የሆነ የሕወሃት ገንዘብ በሕግ አግባብ የውርስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሚመለከተው አካል መተላለፉም ተገልጿል።

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል አቶ ዓለምአንተ አግደው እንደገለጹት ሕገ-ወጥ ቡድኑ ሲቆጣጠራቸው በነበሩና ለሕገ-ወጥ አላማው ሊጠቀምባቸው ይችላል በሚል በተጠረጠሩ ድርጅቶች እንዲሁም በጦርነት በተሳተፉ የጦር መኮንኖችና ሌሎች ባለስልጣናት ላይ በተደረገ የሃብት ክትትልና ምርመራ ውጤታማ ሥራዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት አገራቸው ኢትዮጵያን ከድተው ከሕወሃት ጋር በመሰለፍ በጦርነት የተሳተፉ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎች ገንዘብና ሃብት ላይ በተደረገ ክትትልና ማጣራት ሥራ በድምሩ ከ54.2 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም ሌሎች ብዛት ያላቸው ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲታገድ ተደርጓል።

በኤፈርት/ት.ም.ዕ.ት ሥር በሚተዳደሩ እና ተያያዥ የሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች ላይ በተከናወነ የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ በድምሩ ከ4.2 ቢሊዬን ብር በላይ በፍ/ቤት ትዕዛዝ በማሳገድ እና ግምታቸው ከ 2 ቢሊዬን ብር በላይ የሆኑ 179 የደረቅና የፈሳሽ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ለማሸሽ ጥረት ሲያደርጉ የፍ/ቤት ትዕዛዝ በማውጣትና የጋራ የሕግ ትብብር ጥያቄ ለጅቡቲ መንግስት በማቅረብ ወደ አገር ማስመለስ ተችሏል ነው የተባለው።

በዚህም ህገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የኤፈርት ድርጅቶችን አስመልክቶ ፍ/ቤት የመጨረሻ ውሳኔ አስኪሰጥ ድረስ በፍ/ቤት በተሾሙ ገለልተኛ ባለ አደራ ቦርድ ስር ሆነው ለሕጋዊ አላማ ብቻ እንዲሰሩ ክትትል እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።