የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለመንግሥታቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ግልጽ ደብዳቤ ፃፈ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ናዛት ካን፣ ለሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት እንዲሁም ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባቼሌት ግልጽ ደብዳቤ ፃፈ።
ኮሚሽኑ በጻፈው ደብዳቤ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል እስከ ፈረንጆቹ ኅዳር 3 ቀን 2021ድረስ የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሌላ አካል በድጋሚ እንዲጣራ ማድረግ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት የተካሄደውን ምርመራ እውቅና መንፈግ ነው ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ ምርመራ ተደርጎ በሪፖርት የቀረበውን ጉዳት በሌላ አካል ከማስደገምና ሂደቱን ከማጓተት፣ ቀደም ብሎ በወጣው የምርመራ ሪፖርት መሰረት ተጎጂዎች እንዲያገግሙ፣ ወደ ተፈናቀሉበት ቦታ እንዲመለሱ እንዲሁም እንዲካሱ ብሎም ወንጀል የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ መሠራት ነበረበትም ብሏል በደብዳቤው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በደብዳቤው የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እንደገና ይጣራ ከተባለ አጥፊዎቹ አካላት የፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመካድና እና ኮሚሽኑ የሰራውን ምርመራ ለማጣጣል እድል ከመስጠቱም ባሻገር የኮሚሽኑን ተግባር ዝቅ የሚያደርግ ይሆናል ማለቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።