የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኮፐንሀገን ከተማ በድጋሚ በረራ ሊጀምር ነው

ጥር 17/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዴንማርክ ኮፐንሀገን ከተማ ከግንቦት 14/2015 ዓ.ም ጀምሮ በድጋሚ በረራ ሊጀምር መሆኑን አስታውቋል፡፡

አየር መንገዱ ከማክሰኞ እና እሁድ በስተቀር በሳምንት አምስት ጊዜ ወደ ከተማዋ የመንገደኞች በረራ እንደሚያደርግ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የበረራው መጀመር አየር መንገዱ በሰሜን አውሮፓ እና በምዕራባዊ ስካንዲኒቪያ ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በረራው በአውሮፓና አፍሪካ መሐል ያለውን የአየር ትስስር በማጠናከር ሁለቱ አህጉራት በዲፕሎማሲ፣ በንግድ እና ቱሪዝም ያላቸውን ትብብር የሚያሳልጥ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እ.አ.አ ኅዳር 1999 ወደ ኮፐንሀገን በረራ ጀምሮ ከአራት ዓመት በኋላ አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደነበር በመረጃው ተመላክቷል።