ነሐሴ 3/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬታማ እንዲሆን የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመደገፍ በቅርቡ የ10 በመቶ የካርጎ (የዕቃ ጭነት) ዋጋ ቅናሽ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገና ከጅምሩ የፓን አፍሪካን እሳቤ በመያዝ አፍሪካውያንን ሲያስተሳስር የኖረ ተቋም ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መጀመሩን ለአፍሪካ አገራት ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ይህንንም ሂደት አየር መንገዱ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ አየር መንገዱ አፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመደገፍ በቅርቡ የ10 በመቶ የካርጎ ዋጋ ቅናሽ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ይህም በአህጉሪቱ በንግዱ ዘርፍ የሚካሄደውን የጭነት እንቅስቃሴ በእጅጉ እንደሚያሳልጠው ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በቀጣይም አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ስኬታማ ለማድረግና የአህጉሪቷን እድገት ለማስቀጠል አየር መንገዱ አገራትን በአየር ትራንስፖርት በማስተሳሰር የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ አየር መንገዶች ከሌላው ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ጋር ሲወዳደር በመንገደኞች አገልግሎትም ይሁን በዕቃ ጭነት አገልግሎት ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ሊያድግ ይገባል ነው ያሉት።
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁለቱም የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎቱን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸው በዚህም የሚጠበቅበትን አህጉራዊ ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ነፃ የንግድ ቀጣናው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከርና በአህጉሪቷ አገራት መካከል ሸቀጦች እንዲዘዋወሩ ከማድረግ ባሻገር ለአየር መንገዶች እድገትም ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ነፃ የንግድ ቀጣናው የአህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስቀጠልም ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ገልጸው ይህ አህጉራዊ የነፃ የንግድ ቀጣና ተጨባጭ ውጤት እንደሚያመጣ አገራት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 ወደ ሥራ የገባው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አሁን ላይ በጅምር ደረጃ በተለያዩ አገራት ገቢራዊ እየተደረገ ነው።
ነፃ የንግድ ቀጣና በአግባቡ ገቢራዊ ከተደረገ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2035 የአፍሪካውያንን ገቢ 9 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው ዓለም ባንክ ገልጿል።
ይህም ብቻ ሳይሆን በነፃ የንግድ ቀጣናው በሚፈጠረው የሥራ ዕድል 50 ሚሊየን አፍሪካውያን ከድኅነት እንደሚወጡ የባንኩ ትንበያ ያመላክታል።