የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ 8 አዳዲስ የመንገደኛ አውሮፕላኖች በጥቂት ወራት ውስጥ ይረከባል – መስፍን ጣሰው

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን

ነሐሴ 1/2015 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ካዘዛቸው 26 አውሮፕላኖች ውስጥ ስምንቱን በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚረከብ የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

ዋና ስራ አስፈጻሚው 26 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግና ኤርባስ ከተሰኙ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች ጋር ድርድር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ታዲያ ከእነዚህ አውሮፕላኖች ውስጥ አየር መንገዱ ስምንት የመንገደኛ አውሮፕላኖች በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚረከብ ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ የመንገደኞች አውሮፕላኖች በቀጣይ ጊዜያት እንደሚረከቡ ገልጸው አየር መንገዱ ሌሎች ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለመግዛት እቅድ እንዳለው ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም አየር መንገዱ በሰኔ ወር ከቦይንግ ኩባንያ ሊረከባቸው ግዥ የፈጸመባቸው ሁለት አውሮፕላኖችም በመጪው መስከረምና ጥቅምት ወራት እንደሚረከብ ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ አየር መንገዱ በመጪው ጥቅምትና ህዳር ወራቶች ስድስት አዳዲስ ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎች እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ሊጀመሩ ከታሰቡት አዳዲሶቹ የበረራ መዳረሻዎች መካከልም በስፔን ማድሪድ፣ በእንግሊዝ ለንደን-ጋትዊክ፣ በኔዘርላንስ አምስተርዳም፣ በቬትናም ሃኖይና በማዕከላዊ አፍሪካ ባንጓይ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በተያዘው በጀት ዓመት ገቢውን በ22 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ለዚህም የአውሮፕላን ቁጥር መጨመርና የበረራ መዳረሻውን ከማስፋት በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያና የደንበኞች አገልግሎት የማሻሻል ሥራ እያከናወነ መሆኑን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አየር መንገዱን በሌሎችም በርካታ ዘርፎች የሪፎርም ሥራ በማጠናከር የታቀደውን እድገት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት 145 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን 134 ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች አሉት።