ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቀጣይ በጀት ዓመት በ8 ነጥብ 7 በመቶ የሚያድግ ሲሆን የዋጋ ግሽበቱም ወደ ነጠላ አሃዝ ይወርዳል” ሲሉ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ተናገሩ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ እያካሄደው ባለው 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ስብሰባው ለ2014 በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት እያደረገ ይገኛል።
አቶ አህመድ ለምክር ቤቱ አባላት የኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ባለፈው በጀት ዓመት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ማለፉን ገልጸዋል።
“ከነዚህ መካከል የኮቪድ-19 ወረርሺኝን ጨምሮ የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ፈትነውታል” ብለዋል።
በሁለት አሃዝ የተመዘገበ የዋጋ ንረትና የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት የተፈተነው የ2013 በጀት ዓመት ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮችን ተቋቁሞ የ6 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ማስመዝገቡንና የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ 10 ሺህ 80 መድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የተሻለ እድገት እንደሚያስመዘግብ አመላካቾች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
“በዚህም የአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ 8 ነጥብ 7 በመቶ እንደሚሆን የተተነበየ ሲሆን የዋጋ ግሽበቱም ወደ ነጠላ አሃዝ እንደሚወርድ ይጠበቃል” ብለዋል።
የገቢ እቃዎች ዋጋ በ9 ነጥብ 9 በመቶ የሚያድግ ሲሆን የመንግስት ገቢን ለማሳደግም የተሻሻለ አሰራር እንድሚተገበር ገልጸዋል።
የመንግስት ወጪ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ልማቶች ማስፈጸሚያ እንዲውል ክትትል እንደሚደረግ አብራርተዋል።
“በጀቱ በዋናነት፣ ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለጤናና ለከተማ ልማት ዘርፎችና ለሌሎች አንገብጋቢ መስኮች ይውላል” ብለዋል።
ሚኒስትሩ የፕሮግራም በጀትን አስመልከተው በሰጡት ማብራሪያ በአዲሱ በጀት ዓመት አዲስ የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ እንደማይኖር ተናግረዋል።
በ2014 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ሥራዎችና አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች ብር 162 ነጥብ 17 ቢሊየን፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 183 ነጥብ 55 ቢሊዮን እንዲሆን በረቂቅ ደረጃ ቀርቧል።
ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ብር 203 ነጥብ 95 ቢሊየን እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 12 ቢሊየን ረቂቅ በጀት ሆኖ ምክር ቤቱ ቀርቧል።
በ2014 በጀት ዓመት ጠቅላላ የፌዴራል መንግስት ገቢ መጠን የውጭ ዕርዳታን ጨምሮ ብር 435 ነጥብ 9 ቢሊዮን ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን ይህም በያዝነው በጀት ዓመት ይገኛል ተብሎ ከተገመተው ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ24 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት እንዳለው ለማየት ተችሏል።
ከዚህ ገቢ ውስጥ ብር 369 ነጥብ 1 ቢሊዮን (84 ነጥብ 7 በመቶ) የሚሆነው ገቢ ከአገር ውስጥ እንደሚገኝ ታሳቢ የተደረገ ሲሆን ቀሪው ብር 123 ነጥብ 7 ቢሊዮን ከውጭ ብድርና ዕርዳታ የሚገኝ እንደሆነ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።