ግንቦት 02/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ 92 ነጥብ 6 ሜትሪክ ቶን ካርበን መቀነስ እና የደን ሽፋኑን ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ማሳደግ መቻሉ ተገለጸ፡፡
የአካባቢ፣ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተፅእኖ በመቋቋምና ምላሽ በመስጠት የተሸለ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ተናግረዋል።
እስከ 2010 ዓ.ም በተገኘው አሃዝ መሰረት ከግብርና ዘርፍ 5 ነጥብ 73 ሜትሪክ ቶን ካርበን፣ ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ዘርፍ 23 ነጥብ 55 ሜትሪክ ቶን ካርበን፣ ከደን ዘርፍ 15 ሜትሪክ ቶን ካርበን፣ ከትራንስፖርት ዘርፍ 0 ነጥብ 34 ሜትሪክ ቶን ካርበን፣ ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ 0 ነጥብ 017 ሜትሪክ ቶን ካርበን እና ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ 0 ነጥብ 03 ሜትሪክ ቶን ካርበን በድምሩ 92 ነጥብ 6 ሜትሪክ ቶን ካርበን መቀነስ መቻሉንም ጠቁመዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደ የአፈፃፀም ጥናት መሰረት ከ2002 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና ምላሽ ለመስጠት ከ82 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወይም ከ598 ቢሊየን በላይ ብር ወጪ ተደርጓል ተብሏል፡፡
ኮሚሽኑ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ እያደረገ ሲሆን፣ በውይይቱ የከፍተኛ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተወካዮች እንዲሁም በአጋርነት የሚሰሩ የውጭ ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩም በምሁራን ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው የመፍትሔ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
(በሳራ ስዩም)