የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች በወቅታዊ ሀገራዊ የፀጥታ ጉዳዬች ላይ እየመከሩ ነው

ሐምሌ 22/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች በወቅታዊ ሀገራዊ የፀጥታ ጉዳዬች ላይ በልዩ ስብሰባ እየመከሩ ነው፡፡

የኮሚሽነሮች ልዩ ጉባዬ አጠቃላይ የሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታ  በመካከር  ቀጣይ የሚተገበሩ የፀጥታ ስምሪት ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚደረግ ምክክር ነው ተብሏል።

አሸባሪው  የህወሕት ቡድን  በአፋርና በአማራ ክልል እያደረሰ ያለውን ትንኮሳ ለመቀልበስና ሀገሪቱ ወደ ቀደመ ሰላሟ እንድትመለስ ሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ የልዩ ኃይል ፖሊሶችን  በመጀመሪያ ዙር ማሰማራታቸውና መስዋዕትነት እየከፈሉ ሲሆን ለሁለተኛ ዙርም ዝግጅት እያደረጉ ነው ። ሲዳማና ደበቡ ክልል ቀድመው  መላካቸው  ተነግሯል።

የጁንታው ተላላኪዎች የሆኑት በኦሮሚያ ሸኔ በቤንሻንጉልም የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች ችግር ለመፍጠር እየሰሩ ሲሆን የፌደራል ፖሊስ ፀጥታውን ለማስከበርና ሽፍቶችን ለመደምሰስ ከክልል ልዩ ኃይሎች ጋር በጋራ  ሽፍቶች እደመሰሰና በቁጥጥር ስር አያዋለ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተናግረዋል።

ኮምሽነር ጀነራሉ ጁንታው ለ27 አመት ሲዘርፍ የኖረውን ሀብት ለሽብር ቡድኑ ለመጠቀም ስለሚያስብ የዘረፈውን ኃብት ፖሊስ በህግ ቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን ተናግረዋል። በቅርቡ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት በምርመራ እንዳይንቀሳቀስ ተደርጓል 5 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ብረታ ብረትም መያዙን ገልፀዋል።

የፌደራል ፖሊስ በሁመራ ፥ በቆቦና በአፋር ግንባር ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር ጁንታውን እየተፋለመ መሆኑንም ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተናግረዋል።

በልዩ ስብሰባው የሀገሪቱ የፀጥታ ስምሪት ላይ አቅጣጫ ማስቀመጥ፣ የአፋርና የሶማሌ ክልል ግጭት ማስቆምና የጁንታው ህወሓት ሽብር  መጠቀሚያ እንዳይሆን መስራት ላይ አዲስ አበባና ሌሎች ትልልቅ ከተሞች ላይ የጁንታው ተላላኪዎች ሽብር እንዳይፈጥሩ  በቅንጅት መስራት ላይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሏል።

(በምንይሉ ደስይበለው)