የኢትዮ-ሱዳን የህዝብ ለህዝብ ማጠናከሪያ ውይይት ተጀመረ

መስከረም 10/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦችን የህዝብ ለህዝብ የሚያጠናክር የውይይት መድረክ ተጀምሯል።

የመጪው ዘመን ትውልድ የአፍሪካ አንድነትን እንዲያጠናክር ያለመ እና በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተለያዩ ኤምባሲዎች የሚካሄደው የወንድማማችነት ሁነት በአዲስ አበባ ሱዳን ኤምባሲ መካሄድ ጀምሯል።

ዛሬ በተጀመረው ዝግጅት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል እና የዝግጅቱ ዐብይ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ባደረጉት ንግግር ሁነቱ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኘነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይት መረኃ ግብሩ ረጅም ዘመን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኘነት በየወቅቱ በሚፈጠሩ ችግሮች ሳይወሰን የጋራ እሴቶችን በማጉላት በዘላቂነት እንዲጠናከር ለማስቻል አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሱዳን ኤምባሲ አምባሳደር ጀማል አሸር አህመድ በበኩላቸው የሀገራቱን ነባር ግንኙነት ይበልጥ የህዝቦቹን ወዳጅነት እና ትስስር ለማጠንከር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመረኃ ግብሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሱዳን ኮሙዩኒቲ አባላት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ዲፕሎማቶች የቀድሞ አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች መገኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW