የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ በሰላም እንዲፈታና ኢትዮጵያ የያዘችው የሰላም አማራጭ ተገቢ ነው ተባለ

ጥቅምት 8/2014 (ዋልታ) የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ በሰላም እንዲፈታና ኢትዮጵያ የያዘችው የሰላም አማራጭ ተገቢ እንደሆነ ደቡብ ሱዳን ገለፀች።
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ማርቲን ኤሊያ ሉምሮ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ፣ በኅዳሴ ግድብ፣ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር፣ በአሸባሪው ሕወሐት አገር የማፍረስ ሴራ ዙሪያ አትኩረዋል።
የሽብር ቡድኑ ከመንግሥት የቀረበለትን የሰላም ዕድል ባለመቀበል በአማራና አፋር ክልሎች እየፈፀመ ያለውን ወረራና ጥቃት በተመለከተ አምባሳደሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አተገባበር አዎንታዊ ለውጦች የታዩ ቢሆንም በቀሪ ሥራዎች በተለይ የተቀናጀ የፀጥታ ኃይል ለማደረጃት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ መፋጠን እንደሚገባው አምባሳደሩ ገልፀዋል፡፡
ሚኒስትሩ ማርቲን ኤሊያ በበኩላቸው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ በተመለከተ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ጉዳዩን በሰከነ ሁኔታ መያዙ ተገቢ እንደሆነና በሰላም መፍታት ተገቢ መሆኑን ገልፀው ለደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አተገባበር የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
በተለይ የተቀናጀ የፀጥታ ኃይል የማደራጀቱ እንቅስቃሴ የተጀመረ መሆኑንና በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ዕምነት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት፦
የአማርኛ ፌስቡክ ገፃችንን ይወዳጁ ይከተሉ
ከአረብኛ ፌስቡክ ገፃችን ጋርም ይጓዙ
የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
የትዊተር ገፃችንን ይከተሉ
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!