የኢትዮ- ኬንያ መንገድ የኢትዮጵያን የወደብ አማራጭ እንደሚያሰፋ ተገለጸ

የአፍሪካ አህጉር አቋራጭ የፍጥነት መንገድ አካል የሆነውና በቅርቡ የተመረቀው የኢትዮ- ኬንያ መንገድ የኢትዮጵያን የወደብ አማራጭ የሚያሰፋ መሆኑ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ በኩል ከሀዋሳ ሞያሌ 500 ኪሎ ሜትር እና በኬንያ በኩል ደግሞ ከኢሲኦሎ እስከ ሞያሌ የ503 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ተጠናቆ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መመረቁ ይታወሳል።

የአፍሪካ አህጉር አቋራጭ የፍጥነት መንገድ አካል የሆነው መንገድ አዲስ አበባን ከካይሮ፣ ጋቦሮኒ፣ ኬፕ ታውን እና ኬንያ-ሞምባሳ የሚያገናኝ ከመሆኑም ባሻገር ደቡብ ሱዳንን-ከኬንያ ላሙ ወደብ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ነው።

በብሔራዊ ሎጅስቲክ ምክር ቤት የሎጅስቲክ ትራንስፎስሜሽን ጽህፈት ቤት የሎጅስቲክ ባለሙያው አቶ ተመስገን ይሁኔ ለኢዜአ እንዳሉት መንገዱ ለንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ትስስር ካለው ጠቀሜታ ባሻገር በወደብ ተጠቃሚነት የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም የሚያሳድግ ነው።

ግንባታው ሲጠናቀቅ በአንድ ጊዜ 32 መርከቦችን ማስተናገድ የሚችለውን የላሙ ወደብ ለመጠቀም መንገዱ ያለውን ፋይዳም አስረድተዋል።

ወደቡ በተለይ ለደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥም ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።

በተለይም የኢንዱስትሪ መንደር ለሆኑት ሀዋሳ፣ ይርጋለምና ያቤሎ አካባቢዎች ጥሩ አማራጭ በመሆን ጊዜና ገንዘብ ይቀንሳል ብለዋል።

የመንገዱ መገንባት ከትራንስፖርትና ወደብ ታሪፍ አንጻር አማራጭ በመሆን የኢትዮጵያን የወደብ መደራደር አቅም እንደሚያሳድግም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ከማሳደግ በተጨማሪ ምርቶቿን ለአለም ገበያ የማቅረቢያ ዋና ኮሪደር ሆኖ ያገለግላልም ብለዋል።

የመንገዱ መገንባት 3 ቀናትና ከዚያ በላይ ይፈጅ የነበረውን የየብስ ትራንስፖርት ጉዞ ወደ 10 እና 8 ሰአት ዝቅ አድርጎታል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኬንያ በሰላም ማስከበርና በፖለቲካ ዘርፍ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት በምጣኔ ሃብትም የማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም የኢትዮ-ኬንያ መንገድ በተለይ የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

እንደ አምባሳደር ዲና ገለፃ “ሞያሌን የአካባቢው ዱባይ” የማድረግ ፍላጎትና እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

ከሐዋሳ-ሞያሌ የሚዘልቀው 500 ኪ.ሜ መንገድ እና የጋራ ፍተሻ ኬላ የጉምሩክ፣ የኢሚግሬሽን፣ የጤና እና የደረጃ ድርብርብ ፍተሻ የሚያስቀር መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም የጉምሩክ ሥርዓቱን ግልጽ፣ ቀላል እና ቀልጣፋ ያደርገዋል ተብሏል።

አፍሪካን ለማስተሳሰር በህብረቱ በእቅድ የተያዘው የትራንስ አፍሪካ ሃይዌይ መንገድ አካል የሆነው ይህ መንገድ ሌሎች የአፍርካ አገራትንም የሚያስተሳስር ይሆናል።