የኢፌዲሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በባሕሬን ሥራ መጀመሩ ተገለጸ

በባሕሬን የኢፌዲሪ ቆንስል ጄኔራል ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ጀማል በከር ስራቸውን በይፋ ለመጀመር ባሕሬን ማናማ መግባታቸው ተገልጿል።

አምባሳደሩ ባሕሬን ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ ሲደርሱ የባሕሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይና በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አምባሳደር ጀማል ታኅሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ከባሕሬን የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አደራጅ ኮሚቴ አባላት ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡

የሚስዮኑ መከፈት በባሕሬን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተናገሩት አምባሳደር ጀማል፤ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል።

ሁሉም ዜጋ የአገሩ አምባሳደር መሆኑን በመጠቆም ዳያስፖራው ከቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ ጋር በጋራ ተቀራርቦ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

“የሚስዮኑ ዋነኛ ትኩረት ሁሉንም ዜጎች በቅልጥፍና፣ በፍትሃዊነትና በዕኩልነት የሚስተናገዱበትን አሰራር በመዘርጋት ዜጎችን ማገልገል ነው” ብለዋል።

የነበሩ በጎ ስራዎችን በማስቀጠልና ካለፉት ስህተቶች በመማር ውጤታማ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን ማሳካት እንደሚቻል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ለአምባሳደሩና በሚስዮኑ ለተመደቡ ዲፕሎማቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፤ መንግሥት በባሕሬን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ችግር አዳምጦ ሚሲዮን እንዲከፈት ላቀረቡት ጥያቄ በጎ ምላሽ በመስጠቱና የረጅም ጊዜ ህልማቸው እውን በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

የኮሙኒቲ አባላቱ ከቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ጋር በትብብር ለመስራትና ሚስዮኑ አገልግሎቱን እስኪጀምር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም ቃል መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።