የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ምሥረታ ሥነ-ሥርዓትተካሄደ

ሰኔ 20 /2013 (ዋልታ) – በሰሜን ጎንደር ዞን “አለምዋጭ” አካባቢ የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ግንባታ ምሥረታ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ይገኛል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር  ተስፋሁን ጎበዛይ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ በአለም በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ሀገራት አንዷ ናት።

የስደተኞች ጣቢያው መገንባት  የኤርትራ ስደተኞችን ምቹና አስተማማኝ ቦታ በማድረግ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም  በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ የሽመ ልባ እና ህፃፅ የስደተኞች ካምፖች ምቹ ባለመሆናቸው የተነሳ መዘጋታቸውንና ይህን ተከትሎም “አለምዋጭ”  መጠለያ ጣቢያ መገንባት ማስፈለጉን ጠቅሰዋል።

በሚመሰረተው ጣቢያ  በነዚህ ካምፖች የነበሩና ሌሎችን ጨምሮ  እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ስደተኞችን ተቀብሎ  ለማስተናገድ  መታቀዱን አቶ ተስፋሁን አስረድተዋል።

ለሚመሰረተው መጠለያ ጣቢያ 91 ነጥብ 25 ሄክታር መሬት መመቻቸቱንና  በቅርቡ ተገንብቶ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ይጠበቃል።