የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል – ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ

ነሐሴ 7/2015 (አዲስ ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲሆኑ የመሠረተ ልማት ተቋማት እየተሟሉላቸው መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ አስታወቁ።

የቡሌ ሆራ ከተማ የተመሰረተችበት 100ኛ ዓመት ትናንት ተከብሯል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ ነው።

የክልሉ ከተሞች ለሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲሆኑ ነዋሪዎችን ባሳተፈ መልኩ የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን በመሙላት ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

 የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ

ለዚህም ለቡሌ ሆራ ከተማ የተሰጠው የደረጃ ዕድገትና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።

ባለድርሻ አካለት በተለይም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎውን በማጠናከር ለከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችና የመንገድ መሠረተ ልማት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ መናኸሪያን ጨምሮ በአንድ ቢሊየን ብር ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ተጎብኝተዋል።

በበዓሉ ላይ የፌዴራል መንግሥት፣ የክልሉ፣ የዞን ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የአጎራባች ዞኖች የህዝብ ተወካዮች፣ አባገዳዎችና እንግዶች ተገኝተዋል።