የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ
ግንቦት 04/2013 (ዋልታ) – የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ከሁሉም አስቀድሜ እንኳን ለ2013 ዓ.ም ኢድ አልፈጥር በዓል በሠላም አደረሳችሁ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡
የረመዳን ወር በታላቁ የቁርዓን መጽሐፍ ውስጥ ልዩና የተባረከ ወር ነው፡፡ ይህ ወር በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከአላህ ለነቢዩ ሞሐመድ የተሰጠ የመጀመሪያው ምዕራፍ እንደሆነ ይታመናል፡፡
የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች በረመዳን ወር በጾም፣ በሶላት፣ ሥጋዊ ፍላጎቶቻቸው ገትተው ወደ ፈጠሪ በመቅረብ ያሳልፋሉ፡፡
ይህ ወር በሥራ ምክንያት በተለያየ ቦታ ያሉ የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ ተሰብስበው ፈጣሪያቸውን የሚለምኑበትና የሚያመሰግኑበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
የአገራችን የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች፤ የእምነታችሁን ትዕዛዛት ተከትላችሁ ይህን የረመዳን ወር እና የተባረከ ወቅት በጾምና በሶላት አሳልፋችሁ ለኢድ ቀን ስለበቃችሁ አሁንም ደግሜ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡ ኢድ ሙባረክ! ረመዳን የአንድነት ምልክት ነው፡፡ ማንም የእስልምና ኃይማኖች የሚከተል ሰው የአላህን ትዕዛዝ ማክበርና በቁርዓን ውስጥ የተጻፈውን መፈጸም የዘወትር ግዴታው ነው፡፡
በረመዳን ወር በማወቅም ሆነ በመዘናጋት ከሰው ጋር የተጣላ ሰው ከባለጋረው ጋር የሚታረቀበትና ይቅር የሚባባልበት፣ ካለው ሐብት ቀንሶ ሰደቃ በመስጠት የተቸገረውን የሚረዳበትና ለህዝቡ ራሱን በመስጠት የመንፈሳዊ ሕይወት እድገትን የሚያንጸባርቅ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ከሚከተሉት ትዕዛዛት ውስጥ ሸሃዳ አንዱ ነው፡፡
ፈጣሪን ማክበርና መፍራት፣ ትዕዛዛቱን መጠበቅና ሥራውን ማድነቅ ዘወትር የሚከናወን ተግባር ነው፡፡ ሸሃዳ ወይም ፈጣሪን ለማክበር በቀን 5 ጊዜ ሶላት ማድረግ የእምነቱ ተከታዮች መፈጸም ከሚገባቸው ግዴታዎች ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ የረመዳ ወር በጾም ጊዜ የማንጠቀማቸውን በቅርባችን ላሉ ድሆች በማካፈል የጋራ ሕይወትን ማበረታታት የእስልምና ኃይማኖት ለአገራችንና ለዓለም ያበረከተው ትልቅ እሴት መሆኑ በታላቅ አድናቆት የሚታይ ነው፡፡
የተከባራችሁ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ፤
የእስልምና ኃይማኖት ከሚታወቅባቸው ትዕዛዛትና መመሪያዎች ውስጥ እውነትን መናገር፣ ፍትሕን ማረጋገጥና ክፋትን መቃወም በኃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሕብረተሰብ ዘንድ የጋር ዕሴቶች ሆነው የተወሰዱ ናቸው፡፡ ትናንታችን የዚህ መልካም ዕሴት ወራሾች አድርጎናል፡፡ ዛሬም የምንኮራበትና የምንኖረበት ነው፡፡
አገራችንና ዓለማችን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ታላቅ ፈተና ውስጥ ወድቃ በምትገኝበት በዚህ ወቅት የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ህዝባችንና ሌሎችም የአገራችን ህዝቦች ከሁሉም አቅጣጫ ለተጎዱ ወገኖቻችን ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡
ይህም የመደጋገፍና አብሮ የመኖር ዕሴታችን ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎአል፡፡
ስለሆነም የእስልምና እምነት ምሰሶ የሆነውን ድሃውን መርዳትና የተቸገረውን መደገፍ እንዲሁም ለሐቅና ለእውነት መቆም ከቀደመው ትውልድ የወረስን መልካም ሐብታችን በመሆኑ በዚህ እድል ተጠቅመን ይህን ሐበት ይበልጥ እንድናድገው ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በኃይማኖት መመሪያዎቻችንና በህዝባችን ዕሴቶች መሠረት የሰው ልጅ በተፈጥሮ ክቡር ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ምዕራፍ በዓለምም ሆነ በአገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግጭትና አለመግባባት በሰው ልጆች መካከል ትልቅ ቀውስ ሲያስከትሉ እያየን ነው፡፡
ይህ ደግሞ ፈጣሪና የተፈጥሮ ትዕዛዛት መታዘዝ ከመተዋችን የመነጨ ስለመሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ስለሆነም እንደ ኢድ ያሉትን ታላላቅ ክብረ በዓላት በምናከብርበት ወቅት እንደ ህዝብና ምዕመን ያሉንን የመተጋገዝና አብሮ የመኖር ዕሴቶቻችንን ይበልጥ እንዲያድጉ፣ የመረዳዳት የመደጋገፍና የመከባበር መንፈስ በመሃላችን ይጎለብት ዘንድ መስራት እንዳለብን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡፡
በተጨማሪም ኢማሞች፣ ኡስታዞችና የኃይማኖት መሪዎች በአገርና በህዝብ ጉዳዮች ላይ የሚያስተላልፉልን መልዕክቶች በመከታተል እንድንታዘዝና በምንናገርና በምንተገብራቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ሆነን እንድንቀሳቀስ አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ በመጨረሻም ያሰባችሁት እንዲሳካላችሁ፣ የተመገባቸሁ እንዲስማማችሁ፣ የኢድ-አል ፈጥር በዓል የሠላም፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆንላችሁ እመኝላችኋለሁ፡፡
መልካም ክብረ በዓል!
አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መስተዳድር
ግንቦት 2013 ዓ.ም
ፊንፊኔ