ነሀሴ 01/2013 (ዋልታ) – የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በወንጀል መከላከል፣ የወንጀል ምርመራና ፎረንሲክ ሙያ በመጀመሪያ ዲግሪና ዲፕሎማ ያሰለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖች አስመረቀ።
የኮሌጁ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ቶልቻ መገርሳ እንደገለፁት ውስብስብ እየሆነ የመጣውን ወንጀል ለመከላከል በዕውቀት የበቃ የሰው ሃይል በሚያስፈልገን ወቅት ላይ ነው።
በሳይንሳዊ የወንጀል መከላከልና ምርመራ የበቁ የፖሊስ መኮንኖች መገንባት ላይ ኮሌጅ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሌጁ ይህን መሰረት በማድረግ እየረቀቀ የመጣውን ወንጀል ለመከላከል የሚያስችል ዕውቀት መኮንኖችን ለማስታጠቅ እየሰራ መሆኑን ጨምሮ ገልጸዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪ የወንጀል መከላከል ሰልጣኞች ለ2 ሺህ 800 ሰዓት የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና ተከታትለዋል።
በወንጀል ምርመራና ፎረንሲክ የድፕሎማ ሰልጣኞቹ ከ500 በላይ ሰዓታት የተግባርና ንድፈ ሃሳብ ትምህርት መከታተላቸውን ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ኮሌጁ በወንጀል መከላከል በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እያሰተማረ ሲሆን በተመሳሳይ በማኔጅመንት፣ በሰላምና ደህንነት በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“ኮሌጁን ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችለውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ረቂቅ የማቋቋሚያ አዋጅ ለመንግስት ቀርቦ ውሳኔ እየተጠባበቅን ነው” ብለዋል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዋና አቃቢ ህግና የኮሌጁ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሁሴን ዑስማን በበኩላቸው “ፖሊስ በሳይንስና ዕውቀት የተደገፈ የወንጀል መከላከል፣ የምርመራና ፎረንሲክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት አለበት” ብለዋል።
“ያለን ዕውቀት፣ ትምህርትና ልምድ የወቅቱን ውስብስብ የወንጀል ድርጊት ያገናዘበ መሆን አለበት” ነው ያሉት።
“ኮሌጁ የሴቶች ተሳትፎ ላይ አሁንም በትኩረት መስራት አለበት በተለይ ፍትህን ማረጋገጥ የምንችለው ሴቶችን በወንጀል መከላከልና ምርመራ ንቁ ተሳታፊ መሆኑን ሲችሉ ነው”ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት ወንጀል በይዘትም ሆነ በተግባሩ እጅግ የረቀቀ ነው” ያሉት ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ወንጀል የሚፈፀመው በህብረተሰቡ ውስጥ በመሆኑ ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ከህዝቡ ጋር በማስተሳሰር መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ዋና ኢንስፔክተር ዳንኤል ሃይለማርያም እንዳሉት በስልጠና ቆይታቸው ሳይንሳዊ የወንጀል መከላከል ዕውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ረዳት ኢንስፔክተር አብዲ አህመድ እንደገለፁት በስልጠና ቆይታው በወንጀል ምርመራና ፎረንሲክ ለመስራት የሚያስችለውን ዕውቀት እንደቀሰመ ገልጿል።
ለተመራቂዎቹ የማዕረግ ዕድገት በኮሚሽኑ ተሰጥቷቸዋል።