ነሐሴ 11/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ) በሰላም ግንባታና በልማት ላይ በትብብር ለመስራት ዛሬ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የፈረሙት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ናቸው።
በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ርእሰ መስተዳደሩ እንደተናገሩት በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የስራ እድል ለመፍጠርና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ ነው። ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን ጥራትና ብዛት ለማሳደግም እንዲሁ።
የክልል መንግስት ሰላምን አስጠብቆ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ስራዎች ሲያከናውን መቆየቱን አውስተው፤ በተያዘው የበጀት ዓመትም ህብረተሰቡንና የልማት አጋሮችን በማሳተፍ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በሰላም ግንባታና በልማት ስራዎች ላይ እያደረገ ላለው ትብብር ምስጋና ያቀረቡት አቶ ሽመልስ፤ የክልሉ መንግስት ልማትን በማረጋገጥ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እያደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ የልማት ፕሮግራሙ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ተወካይ ቱርሃን ሳላህ በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ ሰላምና እድገት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የልማት መርኃ ግብር ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸው፤ በሰላም ግንባታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ የስራ እድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዞች አቅም ማሳደግ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በስራ እድል ፈጠራ፣ በደን ልማት፣ በፍትህ አካላት አቅም ግንባታ ላይ የልማት ፕሮግራሙ የሚሰራቸው ተግባራት ከክልሉ የልማት እቅድ ጋር የተጣጣመ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ ቶሎሳ ገደፋ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍና የአካባቢ ጥበቃን ጨምሮ ለሌሎች ስራዎች እገዛ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በስምምነቱ መሰረት በቀጣይ የሚከናወኑት ተግባራት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2022 ጀምሮ ለአራት ዓመታት የሚቆይ መሆኑን ጠቁመው፤ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ 35 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።
ለስራውም የሚያግዙ ስድስት ተሽከርካሪዎች ዛሬ ድጋፍ መደረጉን ኢዜአ ዘግቧል።